44.1 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት የወጣቶች ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

በሻሂዳ ሁሴን

ሥራ አጥ ወጣቶችን ከጥገኝነት ማላቀቅ የሚያስችል የሥልጠና ማዕከልን መገንባት ጨምሮ፣ 44.1 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት የ‹‹ዘ ግሪን ላይት ፕሮጀክት›› ይፋ ሆነ፡፡ የሥልጠና ማዕከሉ ሥራ ሲጀምር  በየዓመቱ 100 ሠልጣኞችን እየተቀበለ በአውቶ ሜካኒክ፣ በንግድና በማርኬቲንግ ዘርፍ አሠልጥኖ ራሳቸውን እንዲችሉ እገዛ ያደርጋል፡፡ ፕሮጀክቱን የሚቆጣጠረው የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ አፈጻጸሙን የሚከታተለው ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያና ወርልድ ቪዥን ኮሪያ መሆናቸውን ዓርብ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በልደታ ክፍለ ከተማ ተክለሃይማኖት አካባቢ ግንባታው በይፋ በተጀመረበት ወቅት ተገልጿል፡፡

ግንባታውን በይፋ ያስጀመሩት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ከግማሽ በላይ የኅብረተሰቡ ክፍል ወጣቶች መሆናቸውን፣ እነሱን በልማት ማሳተፍም ለአገሪቱ የዕድገት ግስጋሴ ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የወጣቶቻችንን ችግር ለይቶ በማውጣት አብሯቸው በመሥራት ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ለአገሪቱ ዕድገትና ብልፅግና ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡ በተለይም ሴት ወጣቶችን በማብቃት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ቤተሰብንና ማኅበረሰብን መቀየር ነው፤›› ሲሉ በወጣቶች ላይ ያተኮረው የፕሮጀክቱ ዓላማ፣ አገሪቱ ከምትከተለው ስትራቴጂ ጋር ተስማሚ መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹ዘ ግሪን ላይት ፕሮጀክት›› በሚል መርህ የተጀመረው ፕሮጀክቱ፣ በሥልጠናው የሚሳተፉ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚፈጥር ተወስቷል፡፡

ማዕከሉ ግንባታው በሚመጣው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም እስከ አምስት ዓመት ይቆያል፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ለሌላ ባለድርሻ አካል ተላልፎ ሥራው እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት ለማድረግ ታስቧል፡፡ አስፈላጊው የግብዓት ግዥም በቅርቡ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡ 75 የሚሆኑ ሴቶችም ከወዲሁ በእንጦጦ የእጅ ባለሙያዎች ቡድን አማካይነት እንዲሠለጥኑ ተደርጓል፡፡

‹‹ወጣቱን በኢኮኖሚ ለማብቃት ጊዜ ይወስዳል፡፡ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት ርብርብም ይጠይቃል፡፡ ለዚህም ፕሮጀክት ትግበራና ውጤታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው፤›› ያሉት ቀዳማዊት እመቤት ሮማን፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን የገንዘብና የዓይነት  ድጋፍ የሚያደርጉት ሁለቱ የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ኪያ ሞተርስና ኮይካ ሲሆኑ፣ ድጋፉም ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት የዋለችላቸውን ውለታ ከመክፈል አኳያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

  ደቡብ ኮሪያ በ1950ዎቹ በጦርነት ላይ በነበረችበት ወቅት ከአሜሪካ ቀጥሎ የጦር ዕርዳታ ያደረገችላት ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በጊዜው ብርቱ ክንድ ሆኗት ጦርነቱን በድል እንድታጠናቅቅ የረዳት ከኢትዮጵያ የተላከው የቃኘው ሻለቃ ክፍለ ጦር ነበር፡፡ ይህ በደቡብ ኮሪያውያን ዘንድ እንደ ትልቅ ውለታ ሲወሳ ቆይቷል፡፡ ይህንንም ውለታ ለመመለስ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በመቅረፅ አገሪቱ ከድህነት ለመላቀቅ በምታደርገው ጥረት እገዛ ለማድረግ ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡