‹‹ሥራ ያስጀመርነው ኢትዮ ፔይ ካርድ ለባንኮችም ለተጠቃሚዎችም ወጪ ቆጣቢ ነው››

አቶ ብዙነህ በቀለ፣የኢት ስዊች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ

በአገሪቱ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ለማጐልበት ያስችላሉ የተባሉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተሠራባቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ኃላፊነት ከወሰዱ ተቋማት ውስጥ ደግሞ ኢት ስዊች አክሲዮን ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ ኢት ስዊች የፋይናንስ ተቋማትን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች በእኩል የአክሲዮን ባለድርሻነት 80 ሚሊዮን ብር ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ 300 ሚሊዮን ብር ያሳደገው ኢት ስዊች ወደፊት ሌሎች ተቋማትም ባለአክሲዮን ሆነው ሊካተቱበት እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ በኢት ስዊች አክሲዮን ኩባንያ በኩል ተግባራዊ ይደረጋሉ የተባሉ የተለያዩ ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎቶች ይጠበቃሉ፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ወደ ሥራ የገባው አንድ የባንክ ደንበኛ በያዘው ካርድ በሁሉም ባንኮች ኤቲኤሞች ገንዘብ ማውጣት የሚያስችለውን አሠራር በመተግበር ነው፡፡ ይህንንም አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ መጠቀም የሚያስችል አሠራር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአሠራር ሥልት በመዘርጋት የየትኛውም ባንክ ደንበኛ በፈለገው ኤቲኤም መጠቀም የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል፡፡ በቅርቡም የባንኮች ፖዞች የየትኛውንም ባንክ ደንበኛ ካርድ ተቀብለው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ እንደ ኢት ስዊች ዕቅድ ኤቲኤሞች ገንዘብ ማውጣት ብቻ ሳይሆን መላክንም የጨመረ አገልግሎት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ እንደ ኤቲኤሞቹ ሁሉ ባንኮቹ በኢንተርኔትና በሞባይል ስልክ ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ አገሪቱ የራስዋ የሆነ የክፍያ ካርድ እንዲኖራት ጭምር ዕድል የሰጠው የኢት ስዊች ጅማሬ በጥሬ ገንዘብ የሚከፈሉ ክፍያዎች በካርድ እንዲካሄዱ ለማድረግ፣ እንደ ውኃ ኤሌክትሪክና ሌሎችም ክፍያዎች በዚህ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ያልፋሉ ተብሎም እየተጠበቀ ነው፡፡ የኢት ስዊች ሥራ አጀማመርና አጠቃላይ አሠራሩን በተመለከተ ዳዊት ታዬ የኢት ስዊች አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢት ስዊች ሥራ ጀምሯል፡፡ ሥራውን የጀመረው ደግሞ የአገሪቱ ባንኮች በኤቲኤሞቻቸው በጋራ እንዲሠሩ በማስቻል ነው፡፡ ይህ አዲሱ አገልግሎት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ብዙነህ፡- ኢት ስዊች ያቋቋመውና በቅርቡ ሥራ የጀመረው የኔትወርክና ሲስተም ዋናው የሚሠራው ነገር፣ የአንድ ባንክ ደንበኛ በሌላ ባንክ ኤቲኤም ተጠቅሞ ገንዘብ እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡ የአንድ ባንክ ተጠቃሚ ካርድ ይዞ ደንበኛ ባልሆነው ባንክ ኤቲኤም ካርዱን በመጠቀም ገንዘብ ማውጣት የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ አሠራሩም አንድ ካርድ የያዘ ደንበኛ በደንበኝነት ባልተመዘገበበት ባንክ ኤቲኤም ውስጥ በሚያስገባበት ጊዜ መጀመሪያ የሚጠየቀው ትክክለኛ የባንኩ ተጠቃሚ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ኤቲኤሙ ፒን ይጠይቀዋል፡፡ ፒኑን ያስገባል፡፡ ኤቲኤሙ ውስጥ ካርድ በሚገባበት ጊዜ አንድ የሚያየው ነገር አለ፡፡ ካርዱን የያዘው ሰው ኤቲኤሙን ያስቀመጠው ባንክ ደንበኛ መሆኑን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ከኤቲኤሙ መረጃውን ለኢት ስዊች ይልካል፡፡ ኢት ስዊች ሲስተም ደግሞ መረጃውን ዓይቶ ገንዘብ ከሌለው ይመልሰዋል፡፡ ካለው ይከፍለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ደንበኛ በሌላ ባንክ ኤቲኤም ሲጠቀም  በራሱ ባንክ ኤቲኤም እስካሁን ሲጠቀም ይጠቀምበት በነበረው የሚስጥር ቁጥር ነው? ወይስ ይቀየራል? ሲጠቀምበት የነበረው ካርድስ?

አቶ ብዙነህ፡- አይቀየርም፡፡ የአንድ ባንክ ደንበኛ በየትኛውም ባንክ ኤቲኤሞች መጠቀም ከፈለገ እስካሁን ሲጠቀምበት በነበረው በሚስጥር ቁጥር ነው የሚጠቀመው፡፡

ካርዱም አይቀየርም፡፡ ኢት ስዊች ያቋቋመው ኔትወርክ ነው፡፡ ሁሉንም ባንኮች የሚያያይዝ ነው፡፡ ሁሉም ባንኮች አሁን ባላቸው ካርድ ተጠቅመው ሳይለውጡ በአንዱ ባንክ ኤቲኤም የሌላው ደንበኛ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ይቀጥላል፡፡ ይህንን አገልግሎት ላይ ያለውንና ባንኮች እየተጠቀሙበት ያለውን ካርድ ለመለወጥ ምንም ዓይነት ጥረት አይደረግም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ካርዶች ወደ አንድ ስታንዳርድ እንዲገቡ ይፈለጋል፡፡ ተነባቢነቱ እስከ ተመሳሳይ ስታንዳርድ መያዝ ድረስ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ ቼክን ውሰድ፡፡ አንድ ዓይነት ስታንዳርድ ይዞ የባንኮቹ ስም ብቻ ነው የሚለያየው፡፡ ቼክነቱ የየባንኩ ቢሆንም፣ ስታንዳርዱ ግን አንድ ነው፡፡

ልክ እንደዚህ የኤቲኤም ካርዶችም ወደዚያ መሄድ አለባቸው፡፡ አሁን ያሉት ባንኮች የሚያወጧቸው ካርዶች አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይነት ያለው ስታንዳርድ የተከተሉ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የካርድ ቁጥር አሰጣጥን ስታይ የሁሉም ባንኮች የካርድ አሰጣጥ በአንድ ስታንዳርድ ውስጥ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የቪዛ ካርድን የሚጠቀሙት የቁጥር አሰጣጣቸው በአራት የሚጀምሩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በአምስት የሚጀምሩ አሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮች ደግሞ የቪዛም የማስተር ካርድም ያልሆነ በራሳቸው መንገድ የቀረፁት የቁጥር አሰጣጥ አላቸው፡፡ ስለዚህ የካርድ ቁጥር አሰጣጣቸው ራሱ አንድ መለያ ነው፡፡ የባንኮቹ የቁጥር አሰጣጥ ስታንዳርድ አለመከተሉ አንዱ ከአንዱ ጋር የመደራረብ ዕድል አለው፡፡ ይህ ደግሞ አደጋ አለው፡፡  

ሪፖርተር፡- አደጋ አለው ሲባል እንዴት?

አቶ ብዙነህ፡- መደራረብ ሲባል አንዱ የሰጠው ቁጥር በሌላውም ላይ የመስጠት ዕድል አለው፡፡ እስካሁን ድረስ አላጋጠመንም፡፡ ነገር ግን እንዲህ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ይኼ አደጋ ነው፡፡ ይህንን ቁጥር አሰጣጥ በተመለከተ አይኤስኦ የራሱ ስታንዳርድ አለው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን እኛ አገር የሚታየው ግን የቪዛ ካርድን የሚጠቀሙት ባንኮች የሚያደርጉት የቪዛ የቁጥር አሰጣጥን ሲስተም ይከታተላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የመሰላቸውን ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ወደ አንድ ስታንዳርድ መምጣት አለበት፡፡ የሁሉም ባንኮች የቁጥር አሰጣጥ ስታንዳርድ ሥር ሆኖ ተናባቢ መሆን አለበት፡፡ ወደ አንድ ስታንዳርድ መምጣት ይኖርበታል፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ አሠራር ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ መናበብ አለበት፡፡ ስታንዳርድ ስንል ለምሳሌ ሶኬቶችን ውሰድ፡፡ አንተ ላፕቶፕህን ይዘህ አንድ ቦታ ቻርጅ ለማድረግ ብትሄድ ሶኬትህን ይዘህ አይደለም የምትንቀሳቀሰው፡፡ ምክንያቱም በየትም ቦታ ስታንዳርድ ያለው ሶኬት ስላለ ሰክተህ ትጠቀማለህ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱን ተነባቢነት ለማምጣት ካርዶች በአይኤስኦ ስታንዳርድ መሠረት ሊያሟሉዋቸው የሚገቡዋቸውን ይዘቶች አካተው መቀረፅ ይኖርባቸዋል፡፡ ወደ አፕሊኬሽኑ ስንመጣም በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቺፕ የሌላቸውን ካርዶች ያወጡ ነበሩ፡፡ በቺፕ የሚሠሩት እንኳን አፕሊኬሽኑም የተለያየ ነው፡፡ ካርዶች ተመሳሳይ ስታንዳርድ ሊከተሉ ይችላሉ፡፡ እኛም አራት ዘርፎችን መርጠን እንዲሠራበት እናደርጋለን፡፡ ይህንን ስናወጣ አዲስ ነገር አልጻፍንም፡፡ ዓለም አቀፉ ደረጃ የካርድ ኩባንያዎችን ያቀፈው ጥምረት ተስማምቶ ያስቀመጠው ስታንዳርድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ወደ አንድ ስታንዳርድ ለማምጣት እየሠራችሁ ነው? ያወጣችሁት ካርድስ አገልግሎቱ ምንድነው?

አቶ ብዙነህ፡- ይህንንማ አደረግን እኮ፡፡ ኢትዮ ፔይ የሚባለውን የኢትዮጵያ ካርድ አውጥተናል፡፡ ኢትዮ ፔይ የኔትወርክ ስም ነው፡፡ እኛ በሁሉም ኤቲኤሞች ላይ ኢትዮ ፔይ የሚለውን እንለጥፋለን፡፡ ቪዛ ካርድ እንደሚባለው ሁሉ እኛም ኢትዮ ፔይ አውጥተናል፡፡ እስካሁን ድረስ ቪዛ ካርድ ያላቸው ባንኮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የዳሸን ቪዛ ካርድ ይዘህ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤቲኤም ገንዘብ ማውጣት አትችልም፡፡ አሁን ነው ኢትዮ ስዊች የተፈጠረው፡፡ ኢትዮ ፔይ ካርድ አገራዊ ካርድ ነው፡፡ ካርዶቹም ወደ አንድ ስታንዳርድ መምጣት አለባቸው አልን፡፡ ይህንን ተመሳሳይ የሚያደርግ ካርድ ቢወጣ ጠቃሚ ነው ተብሎ ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ካርድ ግን ከኢትዮጵያ ውጭ ሊሠራ ይችላል?

አቶ ብዙነህ፡- ወደ ሌሎች አገሮች አገልግሎት ይሰጥ ከተባለም አገልግሎቱን ለመስጠት የተዘጋጀ ነው፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፉ ስታንዳርዱን ስለተጠቀምን ከሌሎች አገሮች ጋር ለመሥራትም ያስችላል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮ ፔይ ካርድን ኬንያ ካለው ስዊች ጋር በማገናኘት ልትሠራበት ትችላለህ፡፡ ሁለቱ መንግሥታት ተስማምተው ሊሠሩ የሚችሉት ነው፡፡ ካርዱ ውጭ እንዲሠራ በተለያዩ አማራጮች አገልግሎቱን ልታወጣ ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ አፍሪካ፣ በመካከለኛው አፍሪካ፣ በእስያ ውስጥም ሪጂናል ኔትወርክ አቅራቢዎች አሉ፡፡ በእነዚህ ሪጅናል ኔትወርኮች ተጠቅመህ አገልግሎትህን ልታሰፋ ትችላለህ፡፡ በእኛ አካባቢም ሪጂናል ኔትወርክ ቢቋቋም ኢትዮጵያን ከዚህ ሪጂናል ኔትወርክ ጋር በማገናኘት ከተለያዩ አገሮች ጋር ትገናኛለች፡፡ ወደ ሌሎችም አገሮች ትሄዳለህ ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ እንደ ማስተር ካርድ ካሉ ፕሮቫይደሮች ጋር በመሆን መሥራት የምትችልበትም ዕድል አለ፡፡

እንዲህ ባለው መንገድ አንዳንድ አገሮች እየሠሩበት ነው፡፡ ለምሳሌ ናይጄሪያ ቨርብ የሚባል ካርድ አቋቁመዋል፡፡ ናሽናል ስዊቻቸው አይደለም ይህንን ያቋቋመው፡፡ ኢንተር ስዊች የተባለው ኩባንያ ያቋቋመው ነው፡፡ ቨርብ የናይጄሪያ ካርድ ሆኖ የወጣ ነው፡፡ እነሱ ቨርብ ሥራ ላይ ያዋሉት ልክ እንደ ማስተር ካርድ አገልግሎት ከሚሰጠው ዲስከቨር ከተባለው ኩባንያ ጋር ተስማምተው ነው፡፡ ቨርብ ካርድ ናይጄሪያ ውስጥ ሲሠራ ቨርቭ ነው፡፡ ከናይጄሪያ ሲወጣ ግን እንደ ዲስከቨር ካርድ እንዲሠራና በዲስከቨር ካርድ ኔትወርክ ላይ እንዲሠራ አደረጉት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ግንኙነት በመፍጠርም መሥራት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ህንድ ሩፒ የሚባለውን ካርድ ከአንድ ኩባንያ ኔትወርክ ጋር በመሆን ኢንተርናሽናል ኔትወርክ ላይ ለማውጣት ስምምነት ፈጥራለች፡፡ የእኛንም ካርድ እንዲህ ባለው መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ይህ ኢትዮ ፔይ ካርድ ለብቻው ተዘጋጅቶ እናንተ የምታሠራጩት ነው ማለት ነው?

አቶ ብዙነህ፡- እኛ የምናሠራጨው ሳይሆን እኛ ስታንዳርዱን አውጥተን ‘ፐርሰናላይዜሽን’ ሲስተሙን አዘጋጅተናል፡፡ ባንኮች ሲፈልጉ በኢትዮ ፔይ ካርድ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ባንኮች ቪዛ ካርድ እያወጡ ይሆናል፡፡ ቪዛ ካርዱን ተውት አንልም፡፡ ኢትዮ ፔይ ካርድ ግን ማውጣት ይችላሉ፡፡ ኢትዮ ፔይ ሊመረጥ ይገባል የምንለው ደግሞ ርካሽ በመሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ፔይ ርካሽ ነው የሚባለው ከምን ጋር ተነፃፅሮ ነው?

አቶ ብዙነህ፡- በአነስተኛ ዋጋ ልንገለገልበት የሚያስችለን ነው የሚባለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ አሁን እኔም አንተም እጅ ቪዛ ካርድ አለ፡፡ በዚህ ቪዛ ካርድ መጠቀማችን ለቪዛ ኩባንያ ተከፍሎ ነው፡፡ እኔ ግን ቪዛ ኔትወርክ ላይ አልተጠቀምኩም፡፡ ክፍያው ደግሞ አንዴ ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ይከፈላል፡፡ ኢትዮ ፔይ ስትጠቀም ይህ የለም፡፡ የእኛ ነው፡፡ ልክ ለቪዛ የምትከፍለውን ክፍያ አትከፍልበትም፡፡ ይህ ከሆነ ለምን እንከፍላለን፡፡ ስለዚህ ይኼ ሥራ ያስጀመርነው ኢትዮ ፔይ ካርድ ለባንኮችም ለተጠቃሚዎችም ወጪ ቆጣቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አንድ የባንክ ደንበኛ ኢትዮ ፔይንም ቪዛ ካርድንም ልይዝ እችላለሁ ማለት ነው?

አቶ ብዙነህ፡- ልትይዝ ትችላለህ፡፡ እዚህ ላይ በእኛ ኢትዮ ፔይ ካርድ መጠቀም የሚያስገኘው ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የቪዛን ለመጠቀም ፈቃድ ይሰጥህና ምን ያህል ካርድ እንዳሠራጨህ ሁሉ ይቆጣጠርሃል፡፡ ምክንያቱም ካርድ ባሠራጨህ ቁጥር ቪዛ ካርድ ገቢው እየጨመረለት ስለሚሄድ ይቆጣጠርሃል፡፡ ስለዚህ እንደፈለግክ ልትጠቀምበት አትችልም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሁሉም ባንኮች ተደማምሮ ለደንበኞቻቸው የሰጡት ካርድ ሁለት ሚሊዮን አይሞላም፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ካርድ ተጠቃሚ ያስፈልጋል ብለህ ብታስብ አሁን ያለው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 100 ሚሊዮን ነው ቢባልና አንድ ቤተሰብ አምስት አባላት አሉት ብለህ ብታሰላ 20 ሚሊዮን ቤተሰብ አለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሥሌት በአንድ ቤተሰብ አንድ ካርድ ቢኖር ሕዝቡ ዘንድ ለመድረስ 20 ሚሊዮን ካርድ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቪዛን በዚህ ደረጃ ለማሠራጨት የሚያስችልህ ዕድል የለውም፡፡   

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ብዙነህ፡- አንደኛ ይህንን ያህል ካርዶች በቪዛ ወይም በማስተር ካርድ በኩል ይሠራጭ ቢባል አገሪቷን ከፍተኛ ወጪ ያስወጣታል፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የሚያስከፍል መሆኑ እንደ አገር ጉዳት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮ ፔይ ካርድ አውጥታችኋል?

አቶ ብዙነህ፡- ይህንን እኮ አሁን ጀምረናል፡፡ ሦስት ባንኮች በኢትዮ ፔይ ካርድ ለመሥራት ወስደዋል፡፡ ለኤቲኤም ተጠቃሚዎቻቸው የሚሰጡት ኢትዮ ፔይን ነው፡፡ አሁን እነዚህ ባንኮች ካርድ አታሚ ድርጅቶች ካርዱን አትመው እንዲሰጡዋቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን የሙከራ ካርዱ መጥቶ ሙከራ ተደርጎ ከሌላ ባንክ ገንዘብ እየወጣበት ነው፡፡ በሥራ ላይ የዋለ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ስለዚህ እነዚህ ሦስት ባንኮች የራሳቸውን ካርድ አያወጡም ማለት ነው?

አቶ ብዙነህ፡- በኢትዮ ፔይ ካርድ ነው የሚጠቀሙት፡፡  

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት የኤቲኤም አገልግሎት ያልጀመሩ ባንኮች አሉ፡፡ እነዚህ ባንኮች በዚህ ካርድ አገልግሎት እንዴት ተጠቃሚ ይሆናሉ?

አቶ ብዙነህ፡- እስካሁን ባለን መረጃ ሁሉም ባንኮች ወደ ኤቲኤም እየገቡ ናቸው፡፡ እያዘዙም ነው፡፡ ኤቲኤም የሌለው ባንክ አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢት ስዊች አገልግሎት ጀመረ ብለን ስንናገር ስለ ኤቲኤም ብቻ ነው፡፡ ኢት ስዊች ግን ከዚህም በላይ አገልግሎቶችን አካትቶ ለመሥራት የተቋቋመ ነው፡፡ ከኤቲኤም ውጪ ያሉ ይሠራሉ የተባሉ ሌሎች አገልግሎቶቻችሁ ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

አቶ ብዙነህ፡- ለምሳሌ በኤቲኤም ቢሆን አሁን ያወጣናቸው አገልግሎቶች የተወሰኑ ናቸው፡፡ ነገር ግን በኤቲኤም ላይ በጣም ድጋፍ የምናደርግባቸው አገልግሎቶች አሉ፡፡ በኤቲኤም ገንዘብ ማስተላለፍ፣ የተላከልህን ገንዘብ በኤቲኤም ለመቀበል የሚያስችል አገልግሎቶች አሉ፡፡ የተለያዩ ቢሎችን ለመክፈል የሚያስችሉ አገልግሎቶች ሁሉ አሉ፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ በፖዝ ላይ ወደ ስድስት የተለያዩ አገልግሎቶች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ ተሞክረዋል፡፡ ከዚህ ውጪ በሞባይል የሚሠሩ ሥራዎችም አሉ፡፡ ኤቲኤም ላይ የምንሠራቸውን ሥራዎች በሞባይልም እናከናውናለን፡፡ በማንኛውም ባንክ ፖዝ ላይ ሄደህ ገንዘብ መክፈል የምትችልበትና የምትገዛበት ሙከራ ተደርጐባቸው ያለቀላቸው በመሆኑ በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በሞባይል የሚሠሩ ነገሮች አሉ፡፡ ልክ በኤቲኤም ማሽኑ እንደምንሰጣቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ሁሉ በሞባይልም መጠቀም የሚያስችል ነው፡፡ ለዚህም ሲስተሙ ላይ ሌሎች አገልግሎቶችም ይቀጥላሉ፡፡ እነዚህን ሥራዎች ለመሥራት ግን በባንኮችም በኩል ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ሁሉ እየጠበቀ የሚሄድ ስለሆነ ከዚህ በኋላ በምዕራፍ ሁለት የምንሠራው ነው፡፡ ከአነድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ተግባራዊ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካርድ ከኤቲኤም ገንዘብ ሲወጣ እንደ ገንዘቡ መጠን የአገልግሎት የሚቆረጥ ወይም የሚከፈል ገንዘብ አለ፡፡ ለምሳሌ 500 ብር በኤቲኤም የሚያወጣ 50 ሣንቲም ይከፈላል፡፡ አሁን እናንተ በጀመራችሁት አዲስ አሠራር የንግድ ባንክ ካርድን ይዤ በዳሸን ባንክ ኤቲኤም ገንዘብ ባወጣ ምን ያህል ክፍያ እጠየቃለሁ?

አቶ ብዙነህ፡- አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ደንበኛ በአንድ መቶ ብር 50 ሣንቲም ነው የሚከፍለው፡፡

ሪፖርተር፡- ደንበኛው በ100 ብር 50 ሣንቲም የሚጠየቀው ደንበኛ ከሆነበት ባንክ ውጪ ባለ ኤቲኤም ሲጠቀም ማለት ነው?

አቶ ብዙነህ፡- አዎ፡፡ ደንበኛ በሆነበት ባንክ ኤቲኤም ሲጠቀም የሚከፈለው ባንኮቹ ባወጡት ተመን ነው፡፡ 100 ብር ስታወጣ ከሚጠየቀው 50 ሣንቲም ውስጥ ገንዘቡን የከፈለው ባንክ 25 ሣንቲም ይወስዳል፡፡ ኢት ስዊች ደግሞ ለአገልግሎቱ 25 ሣንቲም ይወስዳል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኢት ስዊች አክሲዮን ኩባንያ ሲመሠረት እንደ ባለአክሲዮን ሆነው የመሠረቱት ባንኮች ናቸው፡፡ ቆይቶ ግን ከባንኮች ሌላ ሌሎች ተቋማት በተለይ ከፋይናንስ ጋር የሚገናኙ ተቋማት አክሲዮኑ ውስጥ ይግቡ ተብሎ ነበር፡፡ ይህ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ብዙነህ፡- አገልግሎት እስክንጀምር ከባንኮች ጋር፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሌሎቹን እያካተትን እንሄዳለን በሚል ነው፡፡ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር ንግግር እየተደረገ ነው፡፡ በደብዳቤ የጠየቁንም አሉ፡፡ እነሱን ማስገባት የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢት ስዊች ዓላማ በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ቦታ ተደራሽ የሆነ የፋይናንስ አገልግሎት ለማዳረስ ስለሆነ እነሱን በቅርቡ እናስገባለን፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ፡፡ እነዚህ የሚሳተፉበት ለሁሉም ገዥ የሚሆን መተዳደሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ባንኮች እዚህ ውስጥ ሲሳተፉ ግዴታቸው ምንድነው? የሚለው በዝርዝር የተቀመጠ ነው፡፡ ይህንን ተስማምተንበት ለብሔራዊ ባንክ ቀርቦ ያፀድቀዋል ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ ሕጉን የሚያስጠብቀው ኢት ስዊች ነው፡፡ ስለዚህ በኢት ስዊች ውስጥ የሚካተቱት እነማን ናቸው? የሚለው ነገር ተለይቷል፡፡ እነዚህ ተሳታፊዎች በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ የኦፕሬተር ፈቃድ የተሰጣቸው ተቋማትና ሌሎች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ፒኤስኤስ እዚህ ውስጥ ተሳታፊ ነው፡፡ ሌሎችም ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለሚሰጣቸው ተቋማት እኛ በኢት ስዊች ውስጥ እያስገባናቸው እንሄዳለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ወደፊት መምጣት አለባቸው ብለን የምንጠብቃቸው አሉ፡፡ ፈቃድ የሚሰጣቸው ከሆነ ልናስገባቸው የምንችላቸው አሉ፡፡ አሁንም የክፍያ አገልግሎት ሥራ ላይ ያሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ እነማንን ልንጠቅስ እንችላለን?

አቶ ብዙነህ፡- ለምሳሌ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት አንዱ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የፖስታ ድርጅቶች አገልግሎት ከክፍያ ሥርዓት ጋር የተያያዙ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ስለዚህ እሱ መግባት እንዳለበት እንጠብቃለን፡፡ ልክ እንደዚሁ በክፍያ ሥራዎች ላይ እየሠሩ ያሉ ተቋማትም አሉ፡፡ እንደነ ለሁሉ፣ ኤምብር፣ ቤልካሽና የመሳሰሉት ሁሉ መካተት አለባቸው ተብለው የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ተቋማት ወደዚህ ሲገቡ ለእነሱም መልካም ዕድል ነው፡፡ በኢት ስዊች በኩል አገልግሎታቸውን ለሁሉም ሊያደርሱ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ እንደገና ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ተናቦ የመሥራት ሥርዓትን እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ሁለተኛ ከማዕከላዊው ምልከታ በሁሉም ላይ  በክፍያ ሥርዓት ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ያሉ ተቋማት የሚሠሩት ሥራ ከተቆጣጣሪው የብሔራዊ ባንክ ዕይታ ውጪ አይሆንም፡፡ የገንዘብ ዝውውሩም በባንኮች በኩል እንዲሆን ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ ተጠቃሚውን ቀልጣፋ ያደርግለታል፡፡ እንደገናም ብዙ ሰዎችን የባንክ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት? የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የመሳሰሉት በዚህ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ክፍያቸው እንዲፈጸም በመደረጉ ነው?

አቶ ብዙነህ፡- አዎ፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች በባንክ አካውንት የምትከፍል ከሆነ ሰዎች የባንክ አካውንት ይከፍታሉ፡፡ ስለዚህ የባንክ አካውንት የሚከፍቱ ከሆነ ደግሞ ለአገሪቷ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ትልቅ መንገድ ይከፍታል፡፡ የክፍያ ሥርዓትን በተመለከተ የአገሪቷ ፖሊሲ ባንክ መር ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ሌሎች ተሳታፊዎች ሲገቡ ከባንክ ጋር ተገናኝቶ በሚደረግ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ነው የሚሄዱት፡፡ ስለዚህ የገንዘብ ዝውውሩ በባንክ ብቻ እንዲካሄድ ያደርገዋል፡፡ በዚህ መንገድ የአገሪቱ የገንዘብ እንቅስቃሴ በባንክ ውስጥ የሚያልፍ ከሆነ ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለሌላ ፍላጎት ገንዘብ ይገኛል ማለት ነው፡፡  ስለዚህ ኢት ስዊች ይህንን መሀል ላይ ሆኖ የማቀላጠፍ ሥራ ያከናውናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢት ስዊች ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎት ለመስጠት በየግል ስዊች ከመግዛት በአንድ ስዊች መጠቀም ያስችላቸዋል፡፡ በአንድ ቦታ የተከማቹ ኤቲኤሞች ይበታተናሉ የሚል እምነት ነበር፡፡ እናንተ ሥራ ጀምራችኋልና አሁን በአንድ ቦታ የተከማቹት የባንኮች ኤቲኤሞች እንደተባለው ይበታተናሉ ተብሎ ይጠበቃል? በዚህ ረገድ የኢት ስዊች ሚናስ ምንድነው?

አቶ ብዙነህ፡- በነገራችን ላይ በዚህ ዙሪያ አንድ ጥናት እየተሠራ ነው፡፡ አንተ ያነሳኸውም ነገር ከተለያዩ አቅጣጫዎች መታየት አለበት፡፡ ለምንድነው ኤቲኤሞች በአንድ ቦታ የሚሰበሰቡት? የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ኤቲኤሞቹ በአንድ ቦታ የሚሰበሰቡት የየራሳቸው ምክንያት አለ፡፡ ቦታውም ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ኤቲኤሞች የተሰበሰቡት በአንድ ሞል (የገበያ ሥፍራ) ቢሆን ምናልባት እንደ አንድ አማራጭ ለባንክ ደንበኞች በአቅራቢያቸው አገልግሎት ለመስጠት ያደረግኸው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባንኮች ደንበኞቻቸው እዚያ አካባቢ ስለሚጠቀሙ ለእነሱ አገልግሎት ለመስጠት ያስቀመጡት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ብዙ ኤቲኤሞች ተቀምጠዋል፡፡ ይህ ኢት ስዊች እየተለመደ በሚሄድበት ጊዜ ግን እዚያ በሚኖረው የገንዘብ ፍላጐት ላይ በመመሥረት የኤቲኤሞቹ ክምችት ወደ ሌላ አካባቢ ይሸጋሸጋል ብለን እንጠብቃለን፡፡ የኤቲኤም ቁጥሩን የሚወስነው እዚያ ያለው የገንዘብ ፍላጐት ነው፡፡ ስለዚህ ሲስተሙ ራሱን በራሱ የሚያስተካክለው ይሆናል፡፡ ሌላው ደግሞ ሆቴሎች አካባቢ ያሉትን ኤቲኤሞች ውሰድ፡፡ ባንኮች በሆቴሎች አካባቢ ኤትኤሞቻቸውን ለምንድነው የሚያስቀምጡት ስትል ምክንያት አላቸው፡፡ ከገንዘብ ማውጣት አገልግሎት በተጨማሪ ትልቁ ፍላጐታቸው ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም ትልልቅ በምንላቸው ሆቴሎች የሚያርፉት የውጭ ዜጐች ስለሆኑ ዓለም አቀፍ ካርድ ይዘው ይመጣሉ፡፡ ሆቴሉ ውስጥ ባለው ኤቲኤም የውጭ ዜጋው ሲጠቀም ገንዘቡ ከአካውንቱ ተቀንሶ በዶላር ታስቦ እዚህ በብር ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ባንኮቹ የዶላር ግዥ እየሠሩ ነው፡፡ አንዱ ሥራቸውም ይኼ ነው፡፡ ይኼ ዋና ነገር ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ባንኮቹ ይወዳደራሉ፡፡ ስለዚህ አንተ እዚህ አስቀምጥ አንተ እዚህ አታስቀምጥ ከማለት ይልቅ ራሱ የሚስተካከልበት ሁኔታ የሚፈጠር ይመስለናል፡፡ እነኚህ ነገሮች በሕግ ብቻ የምትፈታቸው አይደሉም፡፡ በገበያ ጥበቃ የሚፈቱ ነገሮች አላቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- እዚህ ውስጥ ኢት ስዊች አይገባም ማለት ነው?

አቶ ብዙነህ፡- ኢት ስዊች ይህንን አድርጉ አይልም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢት ስዊች በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የተቋቋመ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ ዋነኛ ባለአክሲዮኖቹ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች ናቸው፡፡ ኢት ስዊች ደግሞ የራሱ የሆነ ገቢ አለውና በዓመቱ መጨረሻ ትርፍና ኪሣራ ይኖረዋል፡፡ ሲያተርፍ ባንኮች ትርፉን እንዲከፋፈሉ ይደረጋል? ወይስ መልሰው ኢንቨስት ያደርጋሉ?

አቶ ብዙነህ፡- ይኼ ገና ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ዋናው ዓላማ ትርፍ መውሰድ አይደለም፡፡ ዓላማው ተመጣጣኝ ዋጋ ለደንበኛው መፍጠር ነው፡፡ አንድ ደንበኛ በአነስተኛ ዋጋ እንዲገላገል የሚያስችል ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ኢት ስዊች ከሚያገኘው ትርፍ ላይ ብዙ አግኝቶ ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል እየሰጠ እንደ ቢዝነስ ትርፍ ላይ የሚያተኩር ሳይሆን፣ መጠኑ ከፍ ያለ ብዙ ተጠቃሚ ያለው ሰፊ አገልግሎት እንዲኖር ነው፡፡ ትኩረታችን በጣም ተመጣጣኝ የሆነ ሲስተም መፍጠር ነው፡፡ ይኼ እኛ የምንለው አይደለም፡፡ ባለአክሲዮኖቻችን የሚወስኑት ነው፡፡ የሚወስኑት ቢሆንም በትርፍ ክፍፍሉ ላይ ያተኮረ አይመስለኝም፡፡ ባንኮቹም የበለጠ የሚጠቀሙት ከስፋቱ ነው፡፡