​ደባልነት

በምሕረተሥላሴ መኰንን

ከመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የተመረቁት በ1965 ዓ.ም. ነበር፡፡ የመጀመሪያ ሥራቸው ጎጃም ውስጥ ማስተማር ሆነና ዕቃቸውን ሸክፈው ተጓዙ፡፡ እንደልባቸው ለመኖር የሚያስችል ገንዘብ ስላልነበራቸው እንደሳቸው አዲስ ከነበሩ መምህር ጋር በጋራ ለመኖር ተስማሙ፡፡ ወርኃዊ ወጪያቸውን በመጋራት ምግብና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮችን ማሟላቱን ተያያዙት፡፡ ከደባላቸው ጋር ከሞላ ጎደል እየተግባቡ ጥቂት ወራት አሳላፉ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን በወርኃዊ ወጪ ክፍፍልና በቤት አያያዝ ረገድ ይጋጩ ጀመር፡፡ ተሞክሯቸውን ያካፈሉን አቶ አረዳው ኃይሉ እንደሚናገሩት፣ ደባላቸው አምሽተው መግባት፣፣ ገንዘብ ሳያዋጡ መቅረትና በረባ ባልረባው መጨቃጨቅ ጀመሩ፡፡ አብረው መዝለቅ እንደማይችሉ ሲገነዘቡም ደመወዛቸውን እንደምንም አብቃቅተው ለብቻቸው ለመኖር ወሰኑ፡፡

እህታቸውን ጥየቃ በተደጋጋሚ ወደ ደጃች ውቤ ሰፈር ይሄዱ እንደነበርና፣ በአካባቢው ብዙ ደባሎች እንዳስተዋሉ ይናገራሉ፡፡ እንደሳቸው ከደባሎቻቸው ዘወትር የሚጋጩ እንዳሉ ሁሉ በስምምነት የሚኖሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ዛሬ ላይ ሆነው ወቅቱን ሲያስታውሱት የወጣትነት ግልፍተኝነት ይዟቸው እንጂ ተስማምተው መኖር ይችሉ እንደነበር ይሰማቸዋል፡፡ ይህንን ቢሉም ግን የደባልነት ኑሮ ቀላል አንዳልሆነም ያምናሉ፡፡ እንኳንስ ሰው እግርና እግርም ይጋጫል የሚለውን ብሒል ያጣቅሳሉ፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ደባልነት አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ምርጫነቱ ቢያመዝንም ዛሬ ዛሬ በተለያየ የኑሮ ደረጃ ያሉ ግለሰቦች የአኗኗር ዘዬ እየሆነ ይመስላል፡፡ በተጨናነቁ የመኖሪያ መንደሮች የግላቸውን አልያም የቀበሌ መኖሪያ ቤታቸውን ከፋፍለው በማከራየት በደባልነት የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የተሻለ የሚባል ገቢ ያላቸው ተመሳሳይ አኗኗር የሚከተሉም አሉ፡፡ ጥሩ ወርኃዊ ገቢ ያላቸውና አብረው አፓርትመንት ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኮንዶሚኒየም በጋራ በመከራየትና ወጪያቸውን በመካፈል የሚኖሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች አቅራቢያ ተሰባስበው የሚኖሩ ተማሪዎችም ይጠቀሳሉ፡፡

አንዳንዶች በቅርበት ከሚያውቋቸው ሰዎች ጋር መኖርን ሌሎች ደግሞ እንግዳ የሆኑ ግለሰቦችን ይመርጣሉ፡፡ ደባልነት በበጎ ጎኑ በሰዎች መካከል መልካም ወዳጅነት ይፈጥራል ቢባልም፣ የከፍተኛ መቃቃር መንስኤም ሊሆን ይችላል፡፡ ደባልነት ግላዊ ሕይወታቸውን የሚጋፋ የአኗኗር ዘዬ እንደሆነ የገለጹልን እንዳሉ ሁሉ በተለያየ ምክንያት የሚመርጡትም አይታጡም፡፡

የደባልነት ኑሮን የማይሹ አስተያየት ሰጪዎች የሰዎች ባህሪ የማይጨበጥ በመሆኑ ለብቻ መኖር እንደሚሻል ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል በተለይ አሁን ላለው የኑሮ ውድነት የደባልነት ኑሮን እንደመፍትሄ የሚያስቀምጡ አሉ፡፡ ብቻቸውን መኖር በጣም የሚከብዳቸውና ደባላቸው ማንም ይሁን ማን ሰው ካጠገባቸው እንዳይጠፋ የሚፈልጉም ገጥመውናል፡፡

በግል ሥራ የተሰማራው ያፌት ግዛቸው ከሰባት ዓመት በፊት ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በደባልነት ኖሯል፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ የሚኖሩት ከዩኒቨርሲቲው ራቅ ባሉ ሰፈሮች ነበረ፡፡ ለተቋሙ እንዲቀርባቸውና ከቤተሰብ ተለይቶ መኖርን ለመልመድ በሚል አምስተኛ በር አካባቢ በ250 ብር ቤት ተከራዩ፡፡ ቤቱ ጠባብ ሲሆን፣ የገዙት መጠነኛ ፍራሽ ብቻ ነበር፡፡ የሚማሩት ተመሳሳይ ትምህርት ስለነበር፣ በኅብረት ያጠናሉ፤ ይበላሉ፤ ይዝናናሉ፡፡ ዛሬም ላይ ሆኖ የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በጣም አስደሳች እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡

ከቤተሰብ መለየት የሰጣቸውን ነፃነት ተጠቅመው ያዝናናል ብለው ያመኑበትን ሁሉ በጋራ ያደርጉ ነበር፡፡ ‹‹ፍሬሽ ነበርን፤ ቤታችን ዩኒቨርሲቲው አጠገብ በመሆኑ ቤተ መጻሕፍት ለረዥም ሰዓት ለመቆየት ያመቻል፣ ስንዝናናም በሰፊው ነበር፤ በመካከላችን የማይረሳ ፍቅር ነበር፤›› ይላል፡፡ ከጊዜ በኋላ ከመካከላቸው ሁለቱ ሲጋራ ማጨስና ጫት መቃም ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹ ከደባሎቹ ውጪ ያሉ ጓደኞቻቸውን ወደ ቤቱ ሲጋብዙ ሌሎቹ ቅር ይሰኙ ጀመር፡፡ ቀስ በቀስ ትስስራቸው እየላላ ፍቅራቸውም እየቀዘቀዘ ሄደ፡፡

ያፌት ሲጋራና ጫትን በተደጋጋሚ ቢቃወምም ሰሚ አላገኘም፡፡ አንድ ቀን ሌሊት ከተንተራሰው ትራስ ላይ ሲጋራ ሸቶት ታመመ፡፡ ከዛ ቀን በኋላ ዳግመኛ ወደ ቤቱ አልተመለሰም፡፡ ቤተሰቦቹ ቤት ተመልሶ መኖር የጀመረ ሲሆን፣ አሁንም ከቤተሰቡ ጋር ነው የሚኖረው፡፡ ከቤት ወጥቶ መኖር ፈታኝ ስለሆነም እዛው መቆየትን ይመርጣል፡፡

የደባልነት ኑሮ እርስ በእርስ መደጋገፍና ሕይወትን መጋራት የተማሩበት ቢሆንም፣ ከመጠን በላይ የሆነው ነፃነት አብሮነታቸውን እንዳፈረሰው ይናገራል፡፡ ሰዎች ምንም ቢዋደዱና ቅርርብ ቢኖራቸው ከጊዜ በኋላ የእያንዳንዱ ሰው የሕይወት አቅጣጫ መለወጡ ስለማይቀር የደባልነት ኑሮ ከባድ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በእሱ ዕምነት፣ ተቃራኒ ጾታዎች በተሻለ መንገድ ተግባብተው አብረው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች ፈጽሞ ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ሲኖሩ እንዳየና ከማያውቀው ሰው ጋር መኖር እንደሚያስፈራው ይናገራል፡፡ ሰዎች ግላዊነታቸው ካልተጠበቀ እንኳን ደባልነት ትዳርም ፈታኝ ይሆናል ይላል፡፡

 በተወሰኑ የሥራ አጋጣሚዎች ሰዎች ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር በደባልነት ይኖራሉ፡፡ የአስተዳደጋቸውና የሕይወት ፍልስፍናቸው መለያየት ፈታኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ቆንጂት የኋላእሸት ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ዩጋንዳ ሄዳ የምትሠራበት ዕድል ተፈጥሮ ነበር፡፡ የወሰዳት ድርጅት ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ፕሮግራም ከኔፓል ከምትመጣ ወጣት ጋር አንድ አፓርትመንት ተጋርተው እንደሚኖሩ ባሳወቃት መሠረት ዩጋንዳ እንደደረሰች ከኔፓሊ ደባሏ ጋር አገናኛት፡፡ የሚኖሩበት ቤት ሳሎንና ማብሰያ ክፍል ሲጋሩ መኝታ ቤትና መታጠቢያ ለየራስ ነበር፡፡

የድርጀቱ ሠራተኞች ከዛ ቀደም በደባልነት የኖሩ ወጣቶች መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረ ስለሚያውቁ፣ ኑሯቸውን በተናጠል እንዲያደርጉ መከሯቸው፡፡ ሆኖም ቆንጂትና ደባሏ ገንዘብ እያዋጡ በጋራ ለመመገብ ተስማሙ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የምግብ ምርጫቸውን ልዩነት ማጣጣም ስላልቻሉ ለየብቻ መብላት ጀመሩ፡፡

በመካከላቸው ያለው የባህል ልዩነት ስለነገሮች ያላቸውን ምልከታ የተለያየ እንዳደረገው ትናገራለች፡፡ በአበላል፣ በአነጋገር፣ በአመለካከትና በባህሪ ፈጽሞ ተቃራኒ ቢሆኑም ተቻችለው ለአንድ ዓመት ኖረዋል፡፡ ኔፓሊዋ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዝግጅት ፍቅር ነበራት፡፡ ለአንድ ዕለት የምትሠራውም ሆነ ለአንድ ጊዜ የምታቀርበው ምግብ ብዙ ሰዎች የሚመገቡት እንደሆነ ቆንጂት ታስታውሳለች፡፡ የቻለችውን ያህል በመመገብም ሆነ በማዘጋጀት ደባሏን ለመተባበር ብትሞክርም የሚዘለቅ አልሆነም፡፡ ምግብ ስታዘጋጅ ሙሉ በሙሉ የሷን ዕርዳታ ብትፈልግም ምግብ ማብሰል ለማትወደው ቆንጂት ይህ የሚቻል አልሆነም፡፡ ኔፓሊዋ ወግ አጥባቂ፣ ተጠራጣሪና ብቻዋን ምንም ማድረግ የማትፈልግ ነች፡፡ ምሽት ከሁለት ሰዓት በኋላ መግባት ጉድ ያስብላታል፡፡ የቢሮ ባልደረቦችም ሆኑ ሌሎች እዚያ ያፈሯቸው ወንድ ጓደኞች ቤታቸውን መጐብኘትም ፈጽሞ ልተቀበለው የሚቸግራት ነገር ነው፡፡

ከፊልም ምርጫ አንስቶ እያንዳንዱ ነገር የሷን ፍላጎት እንዲያማክል ትፈልጋለች፡፡ ለምሳሌ ሲኒማ ቤት ሊሄዱ ካሉ ፊልሞች የህንድ ካልሆነ ብላ ትጠይቃለች ትለምናለችም፡፡ ይኼን ሁሉ ችላ ያለፈው የደባልነት፣ ከተለያየ አኗኗር ከመጡ ሰዎች ጋር በጋራ ስለመኖር እንዳስተማራት ትገልጻለች፡፡ በቅርቡ ገርጂ አካባቢ ከረዥም ዓመት ጓደኛዋ ጋር ስቱዲዮ ኮንዶሚኒየም ተከራይተው የደባልነት ኑሮን ለመጀመር እያኮበኮቡ ነው፡፡ የቅርብ ወዳጆቻቸው የደባልነት ኑሮ ጓደኝነታቸውን እንዳያቀዘቅዘው እንደሚሠጉ አስተያየት መሰንዘራቸው ግን አልቀረም፡፡ እሷ በተቃራኒው በቅርብ የሚተዋወቁ ጓደኛሞች አንዳቸው የሌላቸውን ስሜት ጠብቀው እንደሚኖሩ ስለምታምን ብዙ ችግር ይፈጠራል ብላ እንደማትሰጋ ትናገራለች፡፡

የማያውቁትን ደባል ለማግኘት ወደ ድረ ገፅ የሚያመሩ መኖር ደባልነትን ዘመናዊ ገፅታ ያላበሰው ይመስላል፡፡ ፌስቡክን በመሰሉ የማኅበራዊ ድረ ገጾች በመጠቀም ደባል ማግኘት ይቻላል፡፡ ስለሚፈለጉት ሰው ዓይነት ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ቤታቸውን ለደባሎች ለማከራየት በድረ ገጽ ማስታወቂያ የሚያወጡም ተበራክተዋል፡፡

አይሩምሜትስ ዶት ኮም፣ ቤትኪራይ ዶት ኮምና ኤክስፓትአዲስ ዶት ኮም ከድረ ገጾቹ መካከል ናቸው፡፡ ካውችሰርፊንግ ዓለም አቀፍ ድረ ገጽ ሲሆን፣ በተለያዩ አገሮች ቤት ያላቸውና እንግዳ ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ይገኙበታል፡፡ ድረ ገጹ ላይ ስለቤቱ መረጃ በመልቀቅ ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ ደባሎች ያስተናገደው ሔኖክ ጌታቸው ነው፡፡

እሱና ባለቤቱ የሚኖሩበት ሰፊ ግቢ በርካታ ክፍሎች አሉት፡፡ የውጭ አገር ዜጋ  ባለቤቱ ከተለያየ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች በቤታቸው እንዲኖሩ ስትጠይቀው እንግዳ ነገር ሆኖበት ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ሐሳቧን ተቀብሎ ወደ ቤታቸው እንግዶች መጋበዙን ተያያዙት፡፡ ወደ ቤታቸው ስለሚመጡ ሰዎች ማንነት ድረገጹ ላይ የሚያሰፍሩትን መግለጫ በማንበብ ይረዳሉ፡፡

እንግዶች በቤቱ ለመኖር ገንዘብ መክፈል ወይም የተለያየ አግልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምግብ በማብሰል አልያም ቁሳቁሶችን በማደስ የድርሻቸውን የሚወጡ አሉ፡፡ ከተለያዩ አገሮች የመጡና በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ተስተናግደዋል፡፡ ባላቸው ገንዘብ ልክ በግቢው ውስጥ ካሉ ክፍሎች በአንዱ የሚቆዩ ሶፋ ላይ ቀናት የሚያሳልፉም ነዋሪዎች አሉ፡፡

መሰል አኗኗር በሌሎች አገሮች ቢለመድም ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከብድ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ሰዎች አብረው ሲኖሩ አንዳቸው የሌላቸውን ግላዊ ኑሮ መንካት የለባቸውም፡፡ ደባሎች መገናኘት ያለባቸው በጋራ በሚያከናውኗቸው ነገሮች ብቻ እንደሆነ ብዙዎች እንደማይገነዘቡ ይገልጻል፡፡ ከሰው ጋር ያለ ግንኙነት በሩቅ ሲሆን የተሻለ ነው የሚል አስተሳሰብ እንዳለና እሱ ግን እንደማይቀበለው ይናገራል፡፡

እሱና ባለቤቱ ከብዙ ሰዎች ጋር መኖራቸው የተለያየ አገርን ባህልና አኗኗር እንዲያውቁ አስችሏቸዋል፡፡ ደስተኛ እንደሆኑም ይናገራል፡፡ የአኗኗር ዘዬአቸውን ወደ ቢዝነስም ለውጠዋል፡፡ ከደባሎቻቸው መካከል አስቸጋሪ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ቢገጥሟቸውም የጎላ ችግር አላጋጠማቸውም፡፡ ‹‹ቁልፉ ነገር በንግግር ማመን፣ ኃላፊነት መከፋፈልና የሰዎችን የግል ድንበር መጠየቅ ነው፡፡ በሰዎች አላግባብ መጠቀም የሚፈልጉ፣ ዘወትር ትኩረት የሚሹ፣ ተጠራጣሪና አኩራፊም ሰዎች ሊገጥሙ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ሰዎችን እንደ ባህሪያቸው መያዝ ከጊዜ በኋላ ይለመዳል፤›› ይላል፡፡

የደባልነት ኑሮን ሙሉ በሙሉ የምትነቅፈው ሀና መልካም ነርስ ስትሆን፣ ከዓመት በፊት ከስድስት ጓደኞቿ ጋር ሰበታ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ፕሮጀክት አሸንፈው ሰበታ ሲመደቡ አብረው የመኖር ዕድል ስላገኙ በጣም ተደስተው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ሰበታ እየተመላሱ መሥራት ቢችሉም እዛው አብረው መኖርን መርጠው ቤት ተከራዩ፡፡ ለሁለት ወራት ተግባብተው ቢኖሩም የተለያየ ነገር ያጋጫቸው ጀመር፡፡ ከመኮራረፍ የጀመረው አለመግባባት ወደ መሰዳደብና መደባደብም ደረሰ፡፡ ሁሉም ቤቱን በኃላፊነት መምራት ይፈልግ ነበር፡፡ ጥቃቅን ነገሮች እንኳን የፀብ መንስዔ መሆን ጀመሩ፡፡ አንዳቸው ሲተኙ ሌላቸው ሙዚቃ ይከፍታሉ፡፡ በምግብ ምርጫና በገንዘብም ይጣላሉ፡፡ በስተመጨረሻ ፕሮጀክቱን እንኳን ሳይጨርሱ ተለያዩ፡፡ ዛሬ የቀድሞ ጓደኝነታውም ደፍርሷል፡፡

ሀና ከዛ በኋላ ብቻዋን መኖር ጀምራለች፡፡ ብቸኝነትም ደባልነትም የየራሳቸው በጎና መጥፎ ጎን እንዳላቸው ትናገራለች፡፡ ብቸኝነት ጥንካሬን ቢያስተምርም በሕይወት ውስጥ የሚገጥሙና አጋር የሚያስፈልጋቸው ችግሮችን ለብቻ መጋፈጡ ለሷ አስፈሪ ነው፡፡ ሰዎች በደንብ ቢተዋወቁም አብረው ሲኖሩ ቀድሞ ያልታወቀ ፀባያቸው ስለሚወጣ ደባልነት ፈታኝ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ በደባልነት ኑሮ ሳቢያ ጓደኞቿን ማጣቷ ያስቆጫታል፡፡ ድንበራቸውን ጠብቀው ለየብቻ ቢኖሩ በጓደኝነት እንደሚዘልቁ ታምናለች፡፡  ከዚህ በኋላ ከምታገባው ሰው ጋር ካልሆነ ከሌላ ሰው ጋር ላለመኖር መወሰኗንም ትገልጻለች፡፡

 ከሀና ተቃራኒ ተሞክሮ ያላቸው ሰዓሊዎች ለይኩን ናሁሰናይና ታምራት ገዛኸኝ ናቸው፡፡ ራስ መኮንን ድልድይ በሚገኘውና ናስ አርት ገዳም ብለው በሰየሙት መኖሪያቸው ለዓመታት ኖረዋል፡፡ ተመሳሳይ ሙያ ውስጥ መኖራቸው የበለጠ እንዲቀራረቡና እንዲግባቡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ የእያንዳንዱን ቀን ውሏቸውን ፀበል በመጠጣት ይጀምራሉ፡፡ በሥራዎቻቸው እንዲሁም በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ይደጋገፋሉ፡፡ የደባልነት ኑሮ በክፉና በደጉ ከመተጋገዝ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ለይኩን ይናገራል፡፡

ታምራት እንደሚለው፣ የከተሜነት መስፋፋት የብዙዎችን ሕይወት እያቀራረበው ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው መግባባት ኑሯቸውን እንዳቀለለውም ይገልጻል፡፡ ሳይነጋገሩ ስለሚግባቡ አንዳቸው የሌላቸውን ስሜት አይጎዱም፡፡ የመረረ ፀብ ተጣልተውም አያውቁም፡፡ ለይኩን ሁሉም ሰው ደካማ ጎን እንዳለውና ደባልነትን ፈታኝ ሊያደርገው ቢችልም፣ መግባባት ችግሮችን እንደሚፈታ ያምናል፡፡ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱና ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚሉትን ብሒሎች ያጣቅሳል፡፡