​ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በ31.8 ሚሊዮን ብር እንክብካቤ ሊደረግለት ነው

የ12ኛ ምእት ዓመቱ ይምርሀነ ክርስቶስ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙትን ጥንታዊ ሥዕሎችን ለመጠገንና እንዲሁም ያሉበትን ልዩ ልዩ ችግሮች ለማጥናት የሚውል 31.8 ሚሊዮን ብር (150,000 ዶላር)  ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ (Ambassador`s Fund for Cultural Preservation Award) ተገኘ፡፡ ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ቅጥጥባ) ከዓለም የቅርስ ልማት ፈንድ ጋር ዓርብ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የስምምነት ፊርማ አድርጓል፡፡

‹‹ከወራት በፊት ይምርሀነ ክርስቶስን የመጐብኘት ዕድሉ አጋጥሞኛል፡፡ ካለው ረጅም ዕድሜ አንፃር ያለበት ሁኔታ መልካም የሚባል ቢሆንም ልዩ ልዩ ችግሮች እንዳሉበት መገንዘብ ችያለሁ፤›› ያሉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ፓትሪያሺያ ሀስላክ ናቸው፡፡ ቱሪዝም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና በዋሻው ላይ የሚደረገው እድሳትና ጥናት በዘርፉ የማይናቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አክለዋል፡፡

ከቅጥጥባ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ዘለቀ ጋር የተፈራረሙት የዓለም ሐውልቶች ፈንድ (World Monuments Fund) የሰብ ሰሃራን አፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ስቴፈን ባትል፣ ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የመንፈሳዊነት ምልዐት ያለበት በኪነ ሕንፃዊ ውበቱም የበለፀገ መሆኑን አመልክተው ተቋማቸው የቅርሶችን ጥገናና እንክብካቤ በመደገፍ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ የቅድመ ጥገና ጥናቱም 18 ወራት እንደሚፈጅ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድም ቀደም ሲል በውቅር ቤተ ክርስቲያኑ የተደረጉ ጥናቶች ችግሮች ያሉባቸው በመሆኑ ለሚደረገው ተጨማሪ ጥናት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኗ ያደረገውን ድጋፍ ያወደሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ በቅዱስ ላሊበላ ገዳም ለሚገኙት ቤተ ሩፋኤልና ቤተ ገብርኤልም የተደረገው ጥገና አመስግነዋል፡፡ ድጋፉ በተመሳሳይ ለሌሎችም ታሪካዊ ቅርሶች እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

የዓለም ሐውልቶች ፈንድ ከአራት ዓመት በፊት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር ባደረገው የመግባቢያ ስምምነት መሠረት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥበቃና እንክብካቤ ሥራን ለማከናወን ፈቃድ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡  

ከላሊበላ ከተማ 42 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኘውና በዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ከ800 ዓመታት በፊት በንጉሡ ይምርሀነ ክርስቶስ የተቆረቆረው የዋሻ ቤተ ክርስቲያን ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ80 ዓመት እንደሚበልጥ ይነገራል፡፡ የተገነባውም በሐይቅ ላይ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች ገለጻ፣ ቅዱስ ይምርሀነ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን ለማዋቀር ሲሚንቶም ሆነ ሚስማር አልተጠቀሙም፡፡ እንጨቶችን እርስ በርስ በማፈራረግ የተዋቀረ ነው፡፡ በሰባት ሰማያት ምሳሌ የተገነባው የዋሻ ቤተ ክርስቲያኑ በውስጡ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥዕሎች ይገኙበታል፡፡ ከተለያየ የዓለም ክፍል እንደመጡ የሚነገርላቸው ቅዱሳንም አገልግለውታል፡፡ 5,740 የሚሆኑ ቅዱሳን አጽምም ያረፈው በቤተ ክርስቲያኑ ነው፡፡ ሆኖም ከአያያዝ ጉድለትና በዕድሜ ብዛት ምስሎቹ ወይበዋል፡፡ የቅዱሳኑ አፅምም ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡

ዋሻው ለዘመናት መንገድ አልነበረውም፡፡ ለጉብኝትም ሆነ ለአምልኮ የሚመላለሱ ምዕመናን አቀበትና ቁልቁለቱን በበቅሎ ለማቋረጥ ይገደዱ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ያለባትን የመንገድ ችግርም ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክት በቅርቡ ባስገነባው የጠጠር መንገድ መቅረፍ ተችሏል፡፡