​የዘመናት ነፃ አገልግሎት

በሻሂዳ ሁሴን

ወ/ሮ አስቴር ፍሬ ሰንበት ይባላሉ፡፡ 38 ዓመታቸው ሲሆን ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ ከእሳቸው በታች አራት ልጆች አሉ፡፡ ወላጆቻቸው በአንድ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ይሠሩ ነበር፡፡ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የኑሮ ደረጃ የሆኑ ወላጆቻቸውን መርዳት ትልቁ ምኞታቸው ነበር፡፡ ‹‹ሳድግ ዶክተር፣ ፓይለት እሆናለሁ፤›› ግን አላሉም፡፡ እንዲያውም ማንኛውንም ሥራ በመሥራት ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ ይሹ ነበር፡፡ ነገር ግን በነገሮች አለመቃናት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከባድ ሆነ፡፡

በአሥራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ያስመዘገቡት ነጥብ እምብዛም ስለነበር ኮሌጅ መግባት አልቻሉም፡፡ ነገሩ አሳዛኝ ቢሆንም ህልማቸውን ለማሳካት ይጥሩ ጀመር፡፡ በአንድ ድርጅት ውስጥ በፅዳት ሠራተኝነት መሥራት ጀመሩ፡፡ ሥራው ግን አድካሚ ከመሆኑ ባሻገር ደመወዙም በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ ከእሳቸው አልፎ ወላጆቻቸውን ለመደገፍ በቂ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ብዙም ሳይቆዩ ለቅቀው ሌላ ሥራ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡

በዚህ አጋጣሚ ነበር በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሕፃናት ክፍል ውስጥ የመሥራት ዕድል ያገኙት፡፡ ‹‹ጥቁር አንበሳ ያመጡኝ እናቴና አክስቴ ነበሩ፡፡ ሥራውም በሆስፒታሉ በሕክምና ላይ የሚገኙ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናትን መንከባከብ ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ አስቴር በሆስፒታሉ ማገልገል የጀመሩት መስከረም 7 ቀን 1984 ዓ.ም. እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በመጀመሪያ የሥራ ውሏቸው እንግዳ ስሜት ተሰማቸው፡፡ ሕፃናቱ የሚታከሙበት ክፍል ሲገቡ ውስጣቸው ተረበሸ፡፡ በክፍሉ የተለያዩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ስምንት ሕፃናት ተኝተዋል፡፡ ከመካከላቸው የሰባት ዓመት ልጅ የነበረው፣ ነገር ግን እንደ ጨቅላ ሕፃን መንቀሳቀስ፣ መፀዳዳት የማይችል፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ ጭንቅላቱ በጣም ትንሽ የነበረው ሕፃንን ሲመለከቱ ሕፃናቱን ለመንከባከብ ቆረጡ፡፡ በደመወዝ እንደማይቀጠሩ ተረድተዋል፡፡ በሆስፒታሉ የተገኙት ነፃ አገልግሎት ለመስጠት ነበር፡፡

ለሥራው አዲስ ቢሆኑም ለመልመድ ጊዜ አልፈጀባውም፡፡ ቀን ስምንት ሰዓት ገደማ የገቡት ወ/ሮ አስቴር ሕፃናቱን ሲንከባከቡ ቆይተው ወደ ቤት የተመለሱት በማግስቱ ነበር፡፡ አጋጣሚው ምንም እንኳን ቤተሰባቸውን ለመርዳት የነበራቸውን የሚያሳካ ባይሆንም ሕፃናቱን መርዳት መቻላቸው ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋል፡፡

ጠዋት ገብተው ሕፃናቱን ማጣጠብ፣ ልብስ መቀየር፣ መመገብና ሽንት ጨርቅ መቀየር የየዕለት ሥራቸው ሆነ፡፡ በዚህ መልኩ ሲሠሩ ቀናት ተቆጠሩ፡፡ በጐ ሥራቸው መልካም ስሜት ቢፈጥርላቸውም የተለያዩ አሳዛኝ ገጠመኞች ያስተናግዱ ጀመር፡፡

በአንዱ ቀን ከሕፃናቱ ክፍል የደረሱት ማለዳ ሁለት ሰዓት ላይ ነበር፡፡ ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ ከእንቅልፋቸው ነቅተው ስለነበር አጣጥበዋቸው፣ ልብሳቸውን በመቀየር ምግብ ያበሏቸው ጀመረ፡፡ ተኝቶ የቀረውን ሕፃን ግን ሊቀሰቅሱት አልፈለጉም፡፡ እስኪነቃ ድረስ ሌሎች ሥራዎቻቸውን ማከናወን ያዙ፡፡ ልጁ ግን ሳይነቃ ሰዓታት ተቆጠሩ፡፡ ጥበቃቸውን ትተው ሊቀሰቅሱት ሞከሩ፡፡ ሕፃኑ ሊነቃ አልቻለም፡፡ ሁኔታው ግራ ቢገባቸው የሕክምና ባለሙያዎችን ጠሩ፡፡ ለሰዓታት የተኛው ሕፃን ሕይወቱ ማለፉም በሕክምና ባለሙያዎች ተረጋገጠ፡፡ ፍፁም ያልጠበቁት ነገር በመሆኑ ያ ዕለት የሚያደርጉት ጠፍቷቸው አምርረው ያለቀሱበት ነው፡፡

ሕፃናቱን መንከባከብ የሚያስደስታቸው ወ/ሮ አስቴር አብረዋቸው በሚቆዩባቸው ጊዜያት መላመድ እንደሚፈጠር ይህም እንደ እናት እንዲወዷቸው እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ሕክምናቸውን ጨርሰው ወደ ማሳደጊያ ተቋማት አልያም በማደጐ ለሰዎች በሚሰጡበት ጊዜ አጋጣሚው ለሕፃናቱ መልካም ዕድል እንደሆነ ቢገባቸውም ቅር ያሰኛቸዋል፡፡ ሌላ የሚያደርጉት ነገር ባይኖር ‹‹እኔ ሳልኖር እንዲሰጡ አልፈልግም፤›› በማለት ከሆስፒታሉ የሚወጣውን ሕፃን በሙሉ ለመሰናበት ይሞክራሉ፡፡

ሕፃናቱን ከመንከባከብ ውጪ ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎችም ያከናወናሉ፡፡ ማልደው በመግባት በየክፍሉ ተዘዋውረው የጐደለ ነገር እንዳለ ያያሉ፡፡ ‹‹ላውንደሪ ክፍል ልብሶች ካሉ በየክፍሉ እበትናለሁ፡፡ ሻይ ቡና የሚፈልጉ ሐኪሞች ካሉም አፈላላቸዋለሁ፤›› ሲሉ ሕፃናቱን ከመንከባከብ ጐን ለጐን የሚሠሯቸውን ሥራዎች ያብራራሉ፡፡ ዘወትር ማክሰኞና አርብም ለሕክምና ባለሙያዎቹና ለወላጆች ቡና ያፈላሉ፡፡ የወ/ሮ አስቴርን ቡና የለመዱት የክፍሉ ሠራተኞችም ቡና መድረሱን የሚያበስር ደውል ከወ/ሮ አስቴር እንደሰሙ መሰባሰብ ይጀምራሉ፡፡ ደከመኝ ሰለቸኝ እንደማይሉ ብሩህ ገጽታቸው ይናገራል፡፡ ሁኔታቸው የሥራ ትጋት እምብዛም በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ ያልተለመደ ይመስላል፡፡

ለሥራቸው የተለየ ፍቅር ያላቸው ወይዘሮዋ በበዓላት ቀን እንኳ ለማረፍ አይፈቅዱም፡፡ የትኛውንም በዓል የሚያከብሩት በሆስፒታሉ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማሰናዳት፣ ቡና በማፍላትና ሕፃናትን በመንከባከብ ነው፡፡ እንዲህ ከሚያከብሩት ሥራቸውን ለሳምንታት እንዲቀሩ ያስገደዳቸው አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በሥራ ላይ ሳሉ ድንገተኛ ህመም ያጣድፋቸው ጀመር፡፡ ጥቂት ቆይቶ ይሻለኛል ቢሉም በቀላሉ አልተሻላቸውም፡፡ ሥራ ላይ መቆየት ባለመቻላቸው ወደ ቤት ተመለሱ፡፡ ቤተሰቦቻቸውም ወደ ግል ሆስፒታል ወስደዋቸው ሕክምና እንዲያገኙ ረዷቸው፡፡ ነገር ግን በቶሎ ሊድኑ አልቻሉም፡፡ በሽታው ሥር ሰዶ ኖሮ ለአንድ ወር ያህል እንዲተኙ አስገደዳቸው፡፡ አጋጣሚው ረዘም ላሉ ቀናት ከሥራ ገበታቸው እንዲቀሩ አድርጓቸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ እግራቸው ላይ ባጋጠማቸው ህመም ማነከስ ጀምረዋል፡፡ ይሻለኛል በሚል ተስፋ እግራቸውን እየጎተቱ ሥራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡       

በዚህ መልኩ ለ24 ዓመታት ያገለገሉት ወ/ሮ አስቴር ይህ ነው የሚባል የወር ገቢ የላቸውም፡፡ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የነበራቸው ምኞት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ እንደ መደበኛ ሥራቸው አድርገው የሚያዩትን ሥራቸውን ከሰኞ እስከ አርብ ይሠራሉ፡፡ ጠዋት ገብተው እስከ አመሻሽ ይቆያሉ፡፡ አልፎ አልፎ ሁኔታቸው ያሳዘናቸው ግለሰቦች መጠነኛ ገንዘብ ይሰጧቸዋል፡፡ ነገር ግን ለታክሲ እንኳን አይበቃቸውም፡፡

ከሚሠሩበት ቦታ ወደ ሌላ መዘዋወር አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን የወር ደመወዝተኛ ለመሆን ብዙ ሞክረዋል፡፡ ‹‹ደመወዝተኛ ለመሆን የትምህርት ደረጃዬን ለማሻሻል ሞክሬያለሁ፡፡ ለአራት ዓመታት ያህል ሴክሬታሪያል ሳይንስ ተምሬአለሁ፡፡ ነገር ግን አልተሳካልኝም፡፡ የፅዳት ሠራተኛ ለመሆን ሞክሬም ፈተናውን ባለማለፌ ልቀጠር አልቻልኩም፤›› ሲሉ ለመቀጠር ያደረጓቸው ሙከራዎች አለመሳካታቸውን ይናገራሉ፡፡