​ምትክ መድኃኒቶችን ለማቅረብ

በሻሂዳ ሁሴን

ለዘመናዊ የሥነ ተዋልዶ ጤና መድኃኒቶች ጥራታቸው ሳይጓደል ምትክ መድኃኒት በማዘጋጀትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለአፍሪካ አገሮች ተደራሽ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መሥፈርት አሟልተው ጥቅም ላይ ከዋሉት 29 የሥነ ተዋልዶ መድኃኒቶች መካከል፣ ምትክ ያላቸውና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝቡ እየደረሱ ያሉት 19 የሚሆኑት ናቸው፡፡ በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ ለተቀሩት መድኃኒቶች ምትክ በማዘጋጀት በስፋት ተደራሽ ማድረግ በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ባተኮረውና ከግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በቆየው ውይይት 23 የአፍሪካ አገሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሔራን ገርባ እንዳሉት፣ የዐውደ ጥናቱ ትኩረት የእናቶች ጤና ግብአቶችን በተመጣጠነ ዋጋ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግና ይህንንም ለመከወን የሚያግዱ ልዩ ልዩ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ነጥቦችን ለማዳበር ነው፡፡

እንደ ወ/ሮ ሔራን፣ ኢትዮጵያ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበች ሲሆን፣ ለዚህም መንግሥት የትኩረት አቅጣጫውን የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ አድርጐ መሥራቱ፣ አመቺ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣቱ፣ የመድኃኒት አስመጪዎችንና አከፋፋዮችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር መቻሉ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ይሁንና አገሪቱ ከሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ተሽላ ብትገኝም፣ አሁንም ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን በመግታትና ምትክ መድኃኒቶችን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቃታል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ምግብና የመድኃኒት ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣንና በዩኤንኤፍፒኤ ትብብር በተዘጋጀው ዐውደ ጥናትም ለሕዝቡ ተደራሽ ያልሆኑ አዳዲስ መድኃኒቶችን ተደራሽ ማድረግ፣ ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን መግታት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ በስፋት የሚስተዋለው ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውር በተደረጉ ቁጥጥሮች አሁን ላይ መሻሻሎችን ቢያሳይም፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የጥራት ደረጃቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ ለእናቶችና ሕፃናት ጤና የሚያገለግሉ መድኃኒቶች፤ እንዲሁም የቲቢ፣ የኤችአይቪና የወባ በሽታ መድኃኒቶች ሕገወጥ ዝውውር ከሌሎቹ የመድኃኒት ዓይነቶች በተለየ በስፋት እንደሚታይ ወ/ሮ ሔራን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ይህንን ሕገወጥ ተግባር ከሚፈጽሙት መካከል ሕገወጥ መድኃኒት አስመጪዎች፣ ፋርማሲዎችና አከፋፋዮች ይገኙበታል፡፡ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው መድኃኒቶችን የሚያዘዋውሩ ሕገወጥ ግለሰቦችም አሉ፡፡ ይህ ለባለሥልጣኑ ትልቅ ራስ ምታት እንደሆነ የሚናገሩት ወ/ሮ ሔራን፣ ‹‹መድኃኒቶች እንደ ማንኛውም ሸቀጦች አይደሉም፡፡ በባለሙያ ሊያዙ ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሲበላሹ፣ ያለመረጃ ሲሸጡ ይታያል፡፡ መድኃኒት መድኃኒት የሚሆነው ከመረጃ ጋር ሲሰጥ ነው፣ ካልሆነ ግን ኬሚካል ነው፤›› በማለት የችግሩን አደገኛነትና ውስብስብነት ተናግረዋል፡፡

ለአንድ መድኃኒት ከሚገባው የዋጋ ተመን በላይ የሚያስከፍሉ ሕገወጦች መኖርም ሌላው ፈተና ነው፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚገኙ አካላትን የማስፈጸም አቅም አሳድጐ፣ የጤና ግብአቶችን በተፈለገው መጠንና ጥራት ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ሕገወጥ የመድኃኒት ዝውውርን ለመግታት የጤና የባለሙያዎችና የኅብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም አጠራጣሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ወቅት ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀው የስልክ መስመር 8482 ላይ በመደወል ጥቆማ መስጠት ይችላል፡፡

በዚህ መልኩ ጥቆማ ተደርጎበት የተያዘ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ በወንጀል መጠየቅን ጨምሮ እንደየጥፋት ደረጃው ፈቃዱ ይነጠቃል፣ ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ እገዳ፣ እንዲሁም ምርት አቁመው በአዲስ መልክ ማምረት እንዲጀምሩ የሚያስገድድ ቅጣት እንደሚጣልም ወ/ሮ ሔራን አብራርተዋል፡፡