​ልዩ ተሰጥኦን ማንጠር

በሻሂዳ ሁሴን

ስለ ትምህርት ብዙም ግድ ያላት አትመስልም፡፡ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ የተማረችውም በቤተሰቦቿ ግፊት እንጂ የትምህርት ፍቅር ኖሯት አልነበረም፡፡ ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ለመዓዛ ግርማ ከባድ ነበሩ፡፡ ከአምስተኛ ወደ ስድስተኛ ክፍል ስትዘዋወር ግን ለትምህርት የነበራት አመለካከት በተቃራኒው ሆነ፡፡ በትምህርታቸው ጠንካራ ከሚባሉትና በደረጃ ከሚወጡት ተርታም ሆነች፡፡

ጉብዝናዋ ከመምህራኑ የማስተማር ክህሎት ጋር አብሮ የመጣ መሆኑን ‹‹ከስድስትኛ ክፍል ጀምሮ ያስተማሩኝ መምህሮቼ ጎበዝ ነበሩ፤›› ስትል የመምህራኖቹ የማስተማር አቅም ለትምህርት ያላትን አመለካከት እንደቀየረውና ብርቱ እንዳደረጋት ታስታውሳለች፡፡

ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ጂኦግራፊ ከምትወዳቸው የትምህርት ዓይነቶች መካከል ናቸው፡፡ ከሌሎቹ የትምህርት ዓይነቶችም፣ የላቀ ውጤት ታስመዘግብ የነበረው በሦስቱ ነበር፡፡ ለተወሰኑ ዓመታትም ምስጉን ተማሪ ሆና ቆየች፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አገባድዳ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ስትገባ ግን ነገሮች ዳግም መልካቸውን ቀየሩ፡፡ ‹‹ጥሩ ውጤት አስመዝግቤ የነበረው በስፖርትና በአማርኛ ትምህርት ብቻ ነበር፤›› ስትል፣ ሌሎቹ የትምህርት ዓይነቶች ከብደዋት እንደነበር ትገልጻለች፡፡ በአሥረኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና ያስመዘገበችው ውጤት ዝቅተኛ ስለነበር የመሰናዶ ትምህርት ቤት ለመቀላቀልም አልቻለችም፡፡

በመሆኑም በ2003 ዓ.ም. በ10+2 በኤሌክትሪሲቲ የቴክኒክና የሙያ ትምህርት መማር ጀመረች፡፡ በተግባር የተደገፈው የትምህርት አሰጣጥ ትምህርቱን በቀላሉ ለመረዳት አስቻላት፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር በተግባር ስለነበር ትኩረት የሚስብና ቀላል ነበር፤›› የምትለው መዓዛ፣ ቢውልዲንግ ኢንስታሌሽን የሚባለው ትምህርት በተለይ ይቀላት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ከመጀመርያው ጀምሮ ትምህርት በተግባር የታገዘ ቢሆን ምን ያህል ሊቀላት እንደሚችል ትገምታለች፡፡

ለአንድ አገር ዕድገትና ለተለያዩ የምርምር ሥራዎች  ትምህርት መሠረት ነው፡፡  ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ማንኛውም ልጅ የመማር መብትም አለው፡፡ ይሁን እንጂ እንደመብት ተፈጻሚነቱ በተለያዩ ሁኔታዎች ሲስተጓጎል ይታያል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ዕድሜያቸው ለትምህርት የበቃ 67 ሚሊዮን የሚሆኑ ሕፃናት፣ የመማር ዕድል አያገኙም፡፡ የመማር ዕድሉን ከሚያገኙት መካከልም 31 ሚሊዮን የሚሆኑት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳይደርሱ ያቋርጣሉ፡፡ 32 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ  በትምህርት ደካማና የሚደግሙ ናቸው፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ችግሩ እንደሚበረታ የሚያስረዳው አንድ ጥናት፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 33 ሚሊዮን የሚሆኑ ታዳጊዎች፣ የመማር ዕድሉ እንደማይገጥማቸው፣ የመማር ዕድል ከሚያገኙት መካከልም እስከ መጨረሻው የሚዘልቁ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ያሳያል፡፡

ለዚህም ከተማሪዎች በኩል ያለው የመማር ፍላጎትና ነገሮችን በቀላሉ የመረዳት አቅም፣ ከመምህራን በኩል የሚስተዋለው የትምህርት አሰጣጥ ችግር እንዲሁም የትምህርት ቤቶች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎች አቅርቦት እጥረት በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡  ሁኔታውም እንደ መዓዛ ባሉ ተማሪዎች ላይ አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ይስተዋላሉ፡፡  

ባደጉት አገሮች ከመማር ማስተማር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለይቶ ማስተማር፣ ከጽንሰ ሐሳብ ትምህርት ጎን ለጎን ነገሮችን በተግባር በቤተ ሙከራዎች ውስጥ እንዲሞክሩ ማድረግ ከሚጠቀሟቸው ዘዴዎች መካከል ናቸው፡፡

ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለይቶ የማስተማር አሠራር ለበርካቶች ውጤታማነት የበኩሉን ድርሻ እየተጫወተም ይገኛል፡፡ ባደጉት አገሮች ሥርዓቱ ተግባራዊ ከሆነም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

መሰል ትምህርት ቤቶች በአንዳንድ አገሮች እንደ አማራጭ የሚታዩ አይደሉም፡፡ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ከንቃተ ህሊናቸው ጋር ተያይዞ ነገሮችን በፍጥነት የመረዳት፣ በቀላሉ ነገሮችን የማስታወስ ክህሎትን የማዳበር፣ አንዳንድ እውነታዎችን ያለመቀበል፣ በቀላሉ የመሰላቸትና የመሳሰሉት ባህሪያት ያሳያሉ፡፡ በሌላ በኩል ጥናቶች እንደሚያሳዩት 61 በመቶ የሚሆኑት መምህራን ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የማስተማር ብቃት የላቸውም፡፡

ሁኔታዎች ተደማምረው ተማሪዎቹ ትምህርት እንዲጠሉ ያስገድዳቸዋል፡፡ ከ18 እስከ 25 በመቶ የሚሆኑትም ትምህርት ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም በእነሱ የምጥቀት ደረጃና የመማር ፍጥነት ልክ የማስተማር አቅም ያለው ትምህርት ቤት ማቋቋም ለምሳሌ በአሜሪካ፣ ሜሪላንድ ከግዴታ ይቆጠራል፡፡

በሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ ውጤታማ የሆነው አሠራሩ በኢትዮጵያ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በሚል ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ምግባሩ ኢሳያስ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ከወራት በፊት 90 የሚሆኑ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በሒሳብ፣ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪና በባዮሎጂ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ተማሪዎቹ በየካ ክፍለ ከተማ ዙሪያ ከሚገኙ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ ሲሆን፣ በብሔራዊ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ማስመስዝገብ የቻሉም ናቸው፡፡

ቀድሞ ከነበሩባቸው ትምህርት ቤቶች በተለየ ጽንሰ ሐሳቦችን በተግባር የሚማሩበት ቤተ ሙከራዎች እንዲሁም የተሻለ የማስተማር ክህሎት ባሏቸው የኮሌጅ  መምህራን የመማር ዕድሉን አግኝተዋል፡፡ ተቋሙ ከሚያስተምራቸው የሳይንስ ትምህርት ውጪ ያሉትን የትምህርት ዓይነቶች በሳምንት በተወሰኑ ቀናት በወንድራድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ አጋጣሚው ለብዙዎቹ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከማድረጉም ባሻገር አቅማቸውን እንዲጠቀሙበት ልዩ ልዩ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩ ዕድሉን ፈጥሮላቸዋል፡፡

የ16 ዓመቱ በኃይሉ ደጀኔ ዕድሉን ካገኙ ተማሪዎች መካከል ነው፡፡ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ አስመዝግቦ በፕሮግራሙ የተካተተው በኃይሉ፣  የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦችን በተግባር እንዲመለከትና የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠራ አስችሎታል፡፡

‹‹በፊት እንማር የነበረነበት መንገድ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ቤተ ሙከራ የለም የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦችን  በጽሑፍ ብቻ እንማር ነበር፡፡ ይህን እኛም በማንበብ የምናውቀው ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ከመጣን በኋላ የተሟላ ቤተ ሙከራ በመኖሩ፣ ከጽሑፍ ባሻገር በተግባር እንድንሠራና ጠለቅ ያለ ዕውቀት እንዲኖረን አድርጎናል፡፡ የበለጠ ለመሥራትም የሚያነሳሳ ነው፤›› በማለት፣ ዕድሉ የፈጠረለትን መልካም አጋጣሚ ያብራራል፡፡ ዕድሉ ከዚህ ቀደም የነበረውን የፈጠራ ክህሎት እንዲያዳብርና አዳዲስ ዘርፎችን እንዲሞክር ረድቶታል፡፡ ከፈጠራዎቹ መካከል ከወዳደቁ ዕቃዎች የሠራው የቬርሙዳ ትሪያንግል ናሙና ይገኝበታል፡፡

የቬርሙዳ ትሪያንግል ነገሮችን የማስመጥ ሚስጠር የመሬት እምብርት በመሆኑ ከፍተኛ የስበት ኃይል ስላለው፣ ከፍተኛ የውኃ ዑደት የሚደረግበት ቦታ በመሆኑና በአካባቢው ነገሮችን ማስመጥ የሚችል የጋዝ ልቀት በመኖሩ ነው የሚሉ የተለያዩ መላምቶች ይነገራሉ፡፡ ‹‹ሚቴን የሚባለው ጋዝ ነገሮችን የማቆም አቅም አለው፡፡ አረፋ እየሠራ ወደ ላይ የመውጣት ባህሪ ስላለውም ነገሮችን ከማቆም ባለፈ የማስመጥ ፀባይ አለው፤›› የሚለው በኃይሉ፣ ሦስተኛውን መላምት ተንተርሶ የቬርሙዳ ትሪያንግል ናሙና መሥራት እንደቻለ ይናገራል፡፡

አሰልቺ የሆኑ ንድፈ ሐሳቦችን በቤተ ሙከራ ውስጥ በተግባር እንዲመለከቱትና በቀላሉ እንዲረዱም ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ጽዮን ዮሴፍ ትባላለች፡፡ ‹‹ሒሳብ ለብዙ ነገሮች መሠረት ነው፤›› የምትለው ጽዮን ከሌሎቹ የትምህርት ዓይነቶች በተለይ የሒሳብ ትምህርት እንደምትወድ ትናገራለች፡፡ ትምህርት ከብዷት ባያውቅም ከፊዚክስ ትምህርት ኤሌክትሪሲቲና ማግኔቲዝም የተባሉት ንድፈ ሐሳቦች የተንዛዙ ናቸው በሚል አትወዳቸውም፡፡ በሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ፕሮግራም ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መማር ከጀመረች በኋላ ግን፣ ንድፈ ሐሳቦቹን በተግባር እንድታይና በቀላሉ እንድትረዳቸው እንዳስቻላት፣ በዚህም ደስተኛ እንደሆነች ትገልጻለች፡፡

በቤተ ሙከራ የታገዘ የማስተማር ዘዴ በሌላው ዓለም በስፋት ተለምዷል፡፡ ይህም ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹ ተማሪዎችም ተደራሽ ነው፡፡ ነገር ግን በአገር ውስጥ እምብዛም አልተለመደም፡፡ ይህም ተማሪዎቹ በሥራው ዓለም እንግድነት እንዲሰማቸውና በውጤታማነታቸው ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

 በሳይንስ ሼርድ ካምፓስ የፊዚክስ መምህር የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ግርማ እንደሚሉት፣ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ውስብስብ የሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችን በቀላሉ ለመረዳት ይረዳል፡፡ በጽሑፍ ላይ ብቻ የተወሰነ ትምህርት ግን ለብዙዎች ችግር ሲሆን፣  ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎቹ የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን በላቦራቶሪ በተግባር እንዲሞክሩ በማድረግ በቀላሉ እንዲረዱና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ማድረግ ግድ ይላል፡፡

በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከጌልፈንድ ቤተሰብ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የኢንጂነሪንግና የሒሳብ ትምህርት መርሐ ግብሮችን በተለያየ መልኩ የማጎልበት ሥራም እየተሠራም ይገኛል፡፡ በሳይንስ ሼርድ ካምፓስ በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተመሠረተ የክረምት ተደራሽ መርሐ ግብር፣ የሳይንስ ሙዚየም ተጀምሯል፡፡

እሑድ የካቲት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በልምድ ልውውጥ ላይ ያተኮረ የአንድ ቀን አገራዊ ኮንፈረንስ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ፣ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ መንግሥት ለቀረፀው የ70/30 የትምህርት ድልደላ መሰል ፕሮግራሞች ጠቃሚ እንደሆኑ፣ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠንም እንደሚረዱ፣ ባለድርሻ አካላትም ለዘርፉ መስፋፋት የበኩላቸውን እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ሳይንስ ሼርድ ካምፓስ ከሌላው በተሻለ ፍጥነት ጽንሰ ሐሳቦችን የመረዳት አቅም ያላቸውን ተማሪዎች አቅማቸውን ያገናዘበ ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና በያዙት ፍጥነት እንዲጓዙ ለማድረግ ያስችላል፡፡

በሌሎችም ኮሌጆችና ዩኒቨርሰቲዎች ዘንድ ተግባራዊ ቢደረግና ተደራሽነቱ ቢሰፋ ብዙዎችን መርዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም ባሻገር በየትምህርት ቤቱ በተቻለ ሁሉ በቂ የቤተ ሙከራ አገልግሎት በማዘጋጀት እንደ መዓዛ ያሉ ተማሪዎችን ማብቃትና በርካታ ምሁራንን ለማፍራት እንደሚረዳ አያጠያይቅም፡፡