ፍሬ ከናፍር

‹‹የጦር መሣሪያ አምራቾችና አከፋፋዮች ለስደተኞች ፍልሰት መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ደም አፍሳሹን መሣሪያ ትርፍ ገንዘብ ለማጋበስ ሲባል መነገድ ተገቢ አይደለም፡፡››

የሮም ፖፕ ፍራንሲስ፣ በምዕራባውያኑ የዘመን አቆጣጠር መሠረት የተከበረውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ በጸሎተ ሐሙስ ዕለት መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የተናገሩት፡፡ ፖፕ ፍራንሲስ ከሮም ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ካስትልኑዎቮ ዲ ፖርቶ በተባለው የስደተኞች ማዕከል ከ25 የተለያዩ አገሮች ለተውጣጡ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞችና የሂንዱ እምነት ተከታዮች፣ 829 ስደተኞች ካደረጉት ንግግር በተጨማሪ የ12 ስደተኞችን እግር አጥበዋል፡፡ የወንድማማችነት መንፈስ በሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ውስጥ እንዲሠርፅ በተለያዩ ባህሎችና ሃይማኖቶች መካከል የሰላም ምንጭ የሆነውን መግባባት ለመፍጠር ውይይት አስፈላጊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ በዕለተ ፋሲካ መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሮምና ለዓለም ባስተላለፉት መልዕክትም አምስት ዓመት ባስቆጠረው የሶርያ የርስ በርስ ጦርነት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ሁሉ ነፍጣቸውን አስቀምጠው ለሰላምና ለእርቅ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡