አርማውር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በአዲስ አወቃቀር ሊቀጥል ነው

አርማውር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (አሐሪ) ራሱን ችሎ እንዲተዳደር የተዘጋጀው የመዋቅር ማሻሻያ ረቂቅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከሚወጣበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አወቃቀር ሥራውን የሚመራ ይሆናል፡፡

ዶ/ር አብርሃም አሰፋ የኢንስቲትዩቱ ሜዲካል ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ ኢንስቲትዩቱ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ራሱን ያስተዳድራል፡፡ ከውጭ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከመንግሥት በየዓመቱ በጀት ይመደብለታል፡፡ የራሱ ዋና ዳይሬክተርም ይኖረዋል፡፡

አዲሱ አወቃቀር ኢንስቲትዩቱ እስካሁን እያካሄደ ያለውን የምርምር ሥራ አቅጣጫዎች ያዳብራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ለጤና ጥበቃ ተጠሪ ሆኖ በጀት የሚመደብለት መሆኑም ቀጣይነቱን ያረጋግጣል፡፡  

እንደ ዶ/ር አብርሃም ማብራሪያ፣ በ1991 ዓ.ም. የስዊድን፣ የኖርዌይና የኢትዮጵያ መንግሥታት የኢንስቲትዩቱን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የሦስትዮሽ ስምምነት አድርገው ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት ስዊድንና ኖርዌይ የኢንስቲትዩቱን በጀት እንዲችሉ፣ ከሦስቱ አገሮች የተውጣጣው ቦርድ ደግሞ የኢንስቲትዩቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ እንዲመራ ተደርጐ ነበር፡፡

ኖርዌይና ስዊድን ኢንስቲትዩቱን ኢትዮጵያ በባለቤትነት ይዛ ለራሷ በሚበጃት መልክ መጠቀምና በበጀትም ማገዝ እንዳለባት ማሳሰባቸው፣ አወቃቀሩን በተመለከተ ግን መነጋገር እንደሚቻል ሐሳብ በማቅረባቸው ከስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜ የፈጀ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በተከታታይ በተካሄዱት ውይይቶች ላይ አንዳንድ የውይይቱ ታዳሚዎች ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፋዊነቱ እንደተጠበቀ በኢንዶውመንት ነፃ ሆኖ ይንቀሳቀስ የሚል አማራጭ ሲሰነዝሩ፣ እኩሉ ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት ሥር እንዲሆን የሚል ሐሳብ አቀረቡ፡፡

ውይይቱ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር ከተጠቀሰው አማራጭና ሐሳብ ባሻገር ሌሎች አራት ዓይነት አማራጮች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡ አንደኛው አማራጭ በኢትዮጵያ መንግሥት ሥር ሆኖ በሲቪል ሰርቪስ ይካተት የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካል ይሁን የሚሉ ናቸው፡፡ ሦስተኛው የአለርት አካል ሆኖ ይቀጥል ሲል፣ አራተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ራሱን ችሎ ይተዳደር የሚሉ ነበሩ፡፡

በወቅቱ የነበሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስትርም ራሱን የቻለ አድርጐ ለማቅረብ በቂ ምክንያቶች እንደሌሉ፣ የአገሪቱ የምርምር ሥራዎች በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል እንደሚካሄድ በመግለጽ ተጨማሪ ኢንስቲትዩት መፍጠር እንደማያስፈልግ አመለከቱ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን አካል መምራት ከልምድ ማነስና ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት አሳወቀ፡፡

ከብዙ የሐሳብ መንሸራሸር በኋላ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የአለርት ማዕከል ተረክቦት በሲቪል ሰርቪስ ደንብ መሠረት እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡ በዚህም የተነሳ በ1996 ዓ.ም. አለርት ውስጥ የምርምርና የሥልጠና ክፍል ተብሎ እንዲዋቀር ተደረገ፡፡ ተመራማሪዎችና ሌሎችም ባለሙያዎች የመንግሥት ሠራተኛ መሆን ከፈለጉ እንዲቀጥሉ፣ የማይፈልጉ ካሉ ደግሞ ለቅቀው መሄድ እንደሚችሉ ሲነገራቸው ብዙዎቹ ሲለቁ ጥቂቶቹ ግን ቀጠሉ፡፡

የኢንስቲትዩቱ በአልርት ሥር ሆኖ ሲንቀሳቀስ የስዊድን መንግሥት ድጋፉን ሲቀጥል የኖርዌይ ግን ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ድጋፉን አቋረጠ፡፡ በኋላ ላይ ግን ልክ እንደ ስዊድን፣ ኖርዌይም ድጋፉ አጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ሁለቱ አገሮች ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ያነሳሳቸው፣ የአገሪቱ የጤና ሥርዓት እየተጠናከረና በኢኮኖሚያዊ ልማትም ፈጣን ዕድገት እየተመዘገበ መምጣቱና የክፍሉ የምርምር ሥራ ውጤታማ እየሆነ መቀጠሉ ናቸው፡፡

ለአሥራ አንድ ዓመታት ያህል በአለርት ሥር ሆኖ ሲሠራ ለምርምር ተቸግሮ እንደነበር፣ ምክንያቱም የማዕከሉ ተግባር የሆስፒታሉን አገልግሎት በጥራት ማካሄድ፣ ታካሚ መጥቶ ታክሞ እንዲሄድ ማስቻል ሲሆን አሐሪ ደግሞ የሚያተኩረው ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመሆን ምርምር ማካሄድ በመሆኑ ነው፡፡ አንድ ተመራማሪ ማታ አምሽቶ ቅዳሜና እሑድ የትርፍ ሥራ ሠርቶ ክፍያ አለማግኘቱ ደግሞ ሌላው ችግር ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የክፍሉና የማዕከሉ ሥራ ሊገናኝ፣ ሊጣጣምና ቀልጣፋ ሊሆን እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡

መጨረሻ ላይ ግን ለምርምሩ ቀልጣፋነት እንዲያመች የፋይናንስና የግዢ ሥርዓት ራሱ እንዲያከናውን የሚያስችል የውስጥ ነፃነት ተሰጥቶት በዚህ መልኩ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ፤ አሁን ግን ፍፁም የሆነ አስተዳደራዊ ነፃነት የሚያላብሰው መዋቅር መፅደቁ ይህም ለምርታማነቱ የበለጠ አቅም እንደሚፈጥርለት ተናግረዋል፡፡   

አሐሪ ከተቋቋመበት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ 680 ጆርናሎችን እንዳሳተመ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ሳይንቲስቶች የሁለተኛና የዶክትሬት ዲግሪ ሥራዎቻቸውን በአሐሪ እንዳከናወኑ፣ የአሐሪ ከፍተኛ ባለሙያዎች 25 በመቶ የሚሆን ጊዜያቸውን የሚያውሉት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማርና ሌክቸር በማድረግ ነው፡፡

ሜዲካል ዳይሬክተሩን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ ሳይንቲስቶች፣ ሰባት ረዳት ተመራማሪዎች፣ ለላብራቶሪ አገልግሎት የሚውሉ መሣሪያዎችን የሚጠግኑና የሚያሻሽሉ ሁለት ኢንጂነሮችና በአጠቃላይ 64 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም አሉት፡፡

ከዚህም ሌላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለባዮሎጂ ዲፓርትመንትና ለከብት ሕክምና ኮሌጅ ተማሪዎች የቅድመና የድኅረ ምረቃ ሥራዎችን በማከናወን ቁልፍ ሚና እንደተጫወተና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለሜዲካል ፋኩልቲ የውስጥ ደዌ ሕክምና ተማሪዎች የተግባር ኮርስ በመስጠት እንደሚተባበር ዶ/ር አብርሃ አስረድተዋል፡፡

አሐሪ አሁን ያለውን ይህንኑ መጠሪያ ስም ያገኘው ጌርሐርድ ሐኒሪክ አርማውር ሐንሰን ከተባለው የኢንስቲትዩቱ ኃላፊ ከነበረ ኖርዌጃዊ ሐኪም ነው፡፡ በአምስት መቶ ስኩዌር ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ የተመሠረተው አሐሪ ላብራቶሪዎች፣ መጋዘኖች፣ የጉባዔና የእንስሳት ክፍሎች፣ ወርክሾፖች፣ የተሟሉ ዕቃዎች ያሏቸውና በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዘጠኝ የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶችም አሉት፡፡

አሐሪ እንደ ዓለም አቀፉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሆኖ የባዮሜዲካል ምርምር እንዲያካሂድ የተመሠረተው በ1961 ዓ.ም. ሲሆን፣ በኅብረት ያቋቋሙትም የስዊድሽና የኖርዌጂያን ሴቭ ዘ ችልድረን ድርጅቶች፣ ዘ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ በርገንና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸው፡፡