ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሳታፊ ቁጥሩን 42,000 አደረሰ

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የተሳታፊ ቁጥሩን 42,000 አደረሰ

በዓለም የውድድር መድረክ ትልቅ ስምና ዝናን ላተረፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መገኛ ብቻ ሳይሆን በሺዎች ለሚቆጠሩ ‹‹ስፖርት ለጤና›› የሚሉ ሯጮች አትሌቲክስን እንዲያዘወትሩ አስችሏል፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመታት በፊት በ10,000 ተሳታፊዎች ጀምሮ ዘንድሮ 40,000 ደርሷል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፡፡ በ2009 ዓ.ም. ኅዳር ወር ላይ 16ኛውን ዓመታዊ የአሥር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ከ42,000 ተወዳዳሪዎችን እንደሚያሳትፍ ይፋ አድርጓል፡፡ ምዝገባው ከግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሥር ቅርንጫፎችና በታላቁ ሩጫ ዝግጅት ክፍል የሚጀመር መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር ኃይሌ ገብረሥላሴ በተገኘበት፣ ዝግጅት ክፍሉ ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሒልተን በሰጠው መግለጫው እንደተመለከተው፣16ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት ለየት ባለ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅቱን ከማጠናቀቁም ባሻገር ቶታል ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የዝግጅቱ ዋና ስፖንሰር ሆኖ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ የተገኙት በኢትዮጵያ የቶታል ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ላሲና ቱሪ፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውና ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ እየሆነ ከመጣው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት አብረው መሥራት መጀመራቸው ጠቀሜታው ትልቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

16ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ ከምዝገባው ጀምሮ ለየት ያሉ አዳዲስ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ያስታወሱት የዝግጅት ክፍሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርምያስ አየለ በበኩላቸው፣ ምዝገባው ከሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሥር ቅርንጫፎች፣ ማለትም በደምበል አፍሪካ ጎዳና ቅርንጫፍ፣ በሜክሲኮ ደብረወርቅ ሕንፃ ቅርንጫፍ፣ በ22 ማዞሪያ ጎላጎል ታወር ቅርንጫፍ፣ በቻይና አፍሪካ ቲኬ ሕንፃ ቅርንጫፍ፣ በጉርድ ሾላ ቅርንጫፍ፣ በፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ ቅርንጫፍ፣ በአራት ኪሎ ሥላሴ ቅርንጫፍ፣ በመሿለኪያ ጠመንጃ ያዥ ቅርንጫፍ፣ በመርካቶ መሐል ገበያ ቅርንጫፍና በነፋስ ስልክ ቅርንጫፍ የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን በመጠቀም መመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊው በድርጅት ለሚመዘገቡ ደግሞ በታላቁ ሩጫ ቢሮ መስተናገድ ይቻላል ብለዋል፡፡

ዝግጅት ክፍሉ ሌላው አዲስ የሚተገበረውን አሠራር አስመልክቶ የተሳታፊ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና ከኅብረተሰቡ በደረሰው አስተያየት መሠረት፣ ውድድሩን ለሁለት (ዌቭ ስታርት) በመክፈል ቀይና አረንጓዴ ዌቭ የአጀማመር ሥርዓትን እንደሚከተል አብራርቷል፡፡ በዚሁ መሠረት የቀይ ዌቭ ተወዳዳሪዎች ከጠዋቱ 2፡50 የሚጀምሩ ሲሆን በዚህ የሩጫ ሥርዓት የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች አሥር ኪሎ ሜትሩን ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ማጠናቀቅ የሚችሉና አዘውትረው ስፖርት የሚሠሩትን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡ በቀይ ዌቭ ለሚወዳደሩ ተመዝጋቢዎች የመወዳደሪያ ቲሸርት 170 ብር መሆኑም ታውቋል፡፡

የአረንጓዴ ዌቭ ሯጮች እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ውድድሩን የሚጀምሩት 3፡00 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ የዚህኛው መወዳደሪያ ቲሸርት 150 ብር እንደሆነና ውድድሩን ለማጠናቀቅ የሰዓት ገደብ አልተቀመጠለትም፡፡

የተሳታፊ ቁጥሩን በተመለከተ ካለፈው ዓመት 2,000 በመጨመር በድምሩ 42,000 ተወዳዳሪዎች ከአገር ውስጥና የውጭ አገር ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስታወቀው ዝግጅት ክፍሉ፣ ምዝገባው ቀድሞ የተጀመረበት ዋናው ምክንያት የተወዳዳሪዎችን የመወዳደሪያ ቲሸርት መጠንና ዓይነት ለማዘጋጀት እንዲያመች የታቀደ እንደሆነ አመልክቷል፡፡ የመወዳደሪያ ቲሸርቱ ደግሞ ውድድሩ ሦስት ቀን ሲቀረው ከሐሙስ ኅዳር 8 እስከ ቅዳሜ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይሰጣል፡፡