በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የልብና የካንሰር ማዕከል ሊገነባ ነው

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ለሚያሠራው ብሔራዊ የልብና የካንሰር ማዕከል ግንባታ፣ ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

‹‹ፕሮጀክት 555›› ተብሎ የተሰየመውን የዚህኑ ማዕከል የመሠረት ድንጋይ በጋራ ያስቀመጡት፣ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬና የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ  ናቸው፡፡

ዶ/ር ከሰተብርሃን፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከአልጋ ብዛት፣ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ስብጥርና ከስፔሻሊቲ ደረጃዎቻቸው አኳያ በኢትዮጵያ ትልቁ ሆስፒታል እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ በጤናው ዘርፍ ብዙ የተመዘገቡ ውጤቶች ቢኖሩም፣ ከአገልግሎት ጥራትና ሕዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት ከማቅረብ አንፃር ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ይህንንም ለማሻሻል የተለያዩ ዕቅዶችና አሠራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በብሔራዊ የልብና የካንሰር ማዕከል ይሰጣሉ ተብሎ ከሚጠበቁት አገልግሎቶች መካከል አንዱ የቦን ማሮ ትራንስፕላንት ነው፡፡ ይህም አሁን በአገራችን በመድኃኒትና በጨረራ ሕክምና ብቻ እየተሰጠ ያለውን አገልግሎት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ሊሰጥ በሚያስችል መልክ እንደሚያሻሽለው አስረድተዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን፣ አገሪቱ ተላላፊ በሽታዎችን እየተቆጣጠረች ቢሆንም፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ግን እየሰፉ መሆኑንና በአንጻሩ ደግሞ የሕክምናው አገልግሎት ተደራሽ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ የሚደረገው የሕክምና ሥራ የበለጠ እንዲጠናከርና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ቅስቀሳና ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የተቀመጠውም የመሠረት ድንጋይ የዚሁ ቅስቀሳ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮሌጁ ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር ብርሃኔ ረዳኢ፣  የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ 390 የካንሰር ሕክምናና 205 ለልብ ሕክምና የሚያገለግሉ አልጋዎችን የሚይዝ መንታ ሕንፃዎች እንደሚኖሩት ተናግረዋል፡፡ በሰኔ 2008 ዓ.ም. የሚጀመረውን ግንባታው ለማጠናቀቅ የታቀደውም በ44 ወራት ነው፡፡

ኮሌጁ በልዑል ራስ እምሩ ግቢ ውስጥ ባለው ቦታ ላይ እስከ 200 የሚጠጉ የአካዴሚክ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ከ250 እስከ 300 ለሚደርሱ ሬዚዳንት ሐኪሞችና ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩባቸውን ሕንፃዎች ለመሥራት የሚያስችል የአምስት ዓመት ዕቅድ ይዟል፡፡ እስካሁንም 36 አባወራዎችን የሚያስተናግድ ባለ ስድስት ፎቅ ሕንፃ ተጠናቋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014 ይፋ የሆነው የዓለም ጤና ድርጅት እንዳረጋገጠው፣ በኢትዮጵያ በልብ በሽታ ምክንያት የሞቱት 14,728 ወይንም አጠቃላይ ከተመዘገበው ሞት 2.45 በመቶ ነው፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚሞቱትም ወደ 30 በመቶ ይጠጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በካንሰር ምክያት የሚሞቱት ከአጠቃላዩ አራት በመቶ ገደማ ሲሆኑ፣ በየዓመቱ 60,000 አዳዲስ የካንሰር ሕመምተኞች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ በካንሰር ምክንያት የሚሞቱት በኤችአይቪ፣ በወባና በሳንባ በሽታ ከሚሞቱት በቁጥር እንደሚበልጡም ተረጋግጧል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ከሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ በተጨማሪ በሰው ኃይልና በመሣሪያ የተሟሉ የጤና ተቋማት ባለመኖራቸው በማኅበረሰብ ጤና አጠባበቅ ላይ የሚደርሰው ጫናና አደጋ ከፍተኛ ሆኗል፡፡ ለአብነት ያህልም በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ያለው ብቸኛ የካንሰር ማዕከል 6,000 ታካሚዎችን በመከታተል ላይ ያለ ሲሆን፣ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ስድስት ወራት ያህል መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የታካሚዎች 14 በመቶ ያህልም አገልግሎቱን ለማግኘት ወረፋ ይዘው በሚጠባበቁበት ወቅት ለኅልፈት ይዳረጋሉ፡፡

መንታ ሕንፃዎቹ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ፡፡ ሙሉ ሥራውን ሲጀምር 1800 ያህል የጤና ባለሙያዎች የሚኖሩት ይህ ማዕከል፣ በቀን ከ1900 እስከ 2200 ተመላላሽ ታካሚዎች ማስተናገድ የሚችል ይሆናል፡፡ የጤና ባለሙያዎች በአገር ቤትና በውጭ አገር የሚሠለጥኑበትን አግባብም ኮሌጁ ቀይሷል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ፣ በአገሪቱ አሉ ከሚባሉ የጤና ትምህርት ተቋማት አንዱና ወሳኝ በሆኑ የጤና አግባቦች ዙሪያ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ኮሌጁ ባለፈው መስከረምና ጥቅምት ለመጀመሪያ ጊዜ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አካሂዷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም በሌሎች ወሳኝ የጤና ጉዳዮች ላይ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡